ምርጫው ተአማኒ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲካሄድ ሲቪክ ማህበራት የላቀ ሚናቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
ምርጫው ተአማኒ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲካሄድ ሲቪክ ማህበራት የላቀ ሚናቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ
ግንቦት 12/2013 (ኢዜአ) የዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ ተአማኒ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲካሄድ ሲቪክ ማህበራት የላቀ ሚናቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ።
የኢትዮጵያ የሲቪል ማህበራት ድርጅቶች ጥምረት በምርጫ ዝግጅት፣ በድምጽ አሰጣጥና ከምረጫው በኋላ ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን አስቀድሞ መከላከልን ያለመ ውይይት ከአባላቱና ከባለድርሻ አካላት ጋር አካሂዷል።
የውይይት መነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበራት ድርጅቶች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ዶክተር ንጉሱ ለገሰ፤ ምርጫ በሚካሄድበት ወቅት የተአማኒነትና የፍትሃዊነት ጉዳይ ጥያቄን የሚያስነሳና ግጭቶች እንዲከሰቱ መንስኤ እንደሚሆን አብራርተዋል።
በመሆኑም ምርጫ ከመካሄዱ በፊትም ሆነ በኋላ በሚያስፈልጉ ጉዳዮች ላይ ምላሽ ለመስጠት የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ላይ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል።
በተለይም ገለልተኛ ናቸው የተባሉ አካላትና አስፈጻሚነት ላይ የሚሰሩ በጉዳዩ ዙሪያ ግንዛቤያቸው የሰፋና የነቃ መሆን ይጠበቅበታል ነው ያሉት።
ምርጫ ተአማኒ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ሲቪክ ማህበራት የላቀ ድርሻ እንዳላቸውም አንስተዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ምርጫው በሰላማዊ ሁኔ እንዲከናወን የዜጎች ደህንነትና ሰላም ማስፈን ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው ያሉት።
በተጨማሪም ለታዛቢነት የሚመለመሉ የሲቪክ ማህበራት አባላት የተጣራና እውነተኛ መረጃ ላይ መመርኮዝ ይጠበቅባቸዋልም ብለዋል።
የጥምረቱ ዳይሬክተር አቶ አበራ ሃይለማሪያም በበኩላቸው ላለፉት ሳምንታት የነበረውን የመራጮች ምዘገባ ለመታዘብ ከሁሉም የአገሪቱ ክልሎች የተወጣጡ 144 ታዛቢዎችን ማሰልጠን እና ለትዝብት ማሰማራት አንዱ ነበር ብለዋል።
በዚህም እስካሁን 600 የምርጫ ጣቢያዎችን መታዘብ ተችሏል ብለዋል።
ሲቪክ ማህበራቱ ገለልተኛ አካላት እንደመሆናቸው መጠን ከመንግስትም ሆነ ከማህበረሰቡ ያሉትን ክፍተቶች ማሻሻያ እንዲደረግባቸው ለማድረግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሰራ መሆኑንም አንሰተዋል።
ሰላማዊ የምርጫ ሂደት እንዲኖር ለማስቻል የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያደርጉት ክርክርና ንግግር ለግጭት የሚጋብዝ ሳይሆን ነጻ ሃሳበ የሚንሸራሸርበት መሆን ይኖርበታልም ብለዋል።