ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ዘመን ተሻጋሪ ስኬት የሲቪልአቪዬሽን ባለስልጣን ሚና የላቀ እንደሆነ የትራንስፖርት ሚኒስቴር ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ዘመን ተሻጋሪ ስኬት የሲቪልአቪዬሽን ባለስልጣን ሚና የላቀ እንደሆነ የትራንስፖርት ሚኒስቴር ገለጸ
ግንቦት 12 ቀን 2013 (ኢዜአ) ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ዘመን ተሻጋሪ ስኬት የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ሚና የላቀ መሆኑን የትራንስፖርት ሚኒስትር ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ ገለጹ።
ሚኒስትሯ በቦሌ አለም ዓቀፍ አየር ማረፊያ የሚገኝውን የአየር ትራፊክ መቆጣጠሪያ ማማ (ታወር) የማስፋፊያ ግንባታ በዛሬው እለት በመረቁበት ወቅት ባደረጉት ንግግር የኢትዮጵያ አየር መንገድ ደንበኞቹ እምነት እንዲጥሉበት ሲቪል አቪየሽን ባለስልጣን የድርሻውን መወጣት ይጠበቅበታል።
አየር መንገዱ ያለውን ደረጃ ማስጠበቅ ብቻ ሳይሆን ከፍ ብሎ እንዲበር ለማድረግ የጥራት ደረጃውን አስተማማኝ ለማድረግ እንደሚሰራም ጠቁመዋል።
በዚህ ረገድ የሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን የድርሻውን እንዲወጣ የትራንስፖርት ሚኒስቴር አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ወይዘሮ ዳግማዊት ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኮሎኔል ወሰንየለህ ሁነኛው በበኩላቸው "አየር መንገዱ ያለበትን የማያቋርጥ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ተቋቁሞና አሸናፊ ሆኖ እንዲወጣ ያላሰለሰ ጥረት እየተደረገ ነው" ብለዋል።
በዛሬው እለት ለምርቃት የበቃው የአየር ትራፊክ መቆጣጠሪያ ማስፋፊያ ዘርፉን ለማሳደግና ለማዘመን ሚናው የጎላ እንደሆነም ጠቅሰዋል።
በቅርቡም በአራት ቦታዎች ተገንብተው ለአገልግሎት ብቁ ሆነው የተመረቁት የአየር ትራፊክ መቆጣጠሪያ ማማዎች የአቪዬሽን ዘርፉ በየክልሉ በጥራትና በብቃት አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ ማስቻሉን ጠቁመዋል።
በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ዛሬ የተመረቀው የማስፋፊያ ታወር 48 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደተደረገበት ለማወቅ ተችሏል።