የፋሲል ከነማን የእግር ኳስ ክለብን ለማጠናከር የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ሊካሄድ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የፋሲል ከነማን የእግር ኳስ ክለብን ለማጠናከር የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ሊካሄድ ነው
ጎንደር ፤ ግንቦት 12/2013(ኢዜአ) የፋሲል ከነማን የእግር ኳስ ክለብ ለማጠናከር በህር ዳርና ጎንደር የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር እንደሚካሄድ ክለቡ አስታወቀ።
የክለቡ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደባባይ ሙሉጌታ ዛሬ በሰጡት መግለጫ በሁለቱ ከተሞች ለክለቡ ማጠናከሪያ የሚውል 100 ሚሊዮን ብር ገቢ ለማሰባሰብ የሚያስችሉ መርሃ ግብር ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ ነው።
በገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሩ በክልሉና በሀገር አቀፍ ጭምር ነዋሪ የሆኑ ታዋቂ ባለሀብቶችና ነጋዴዎች እንዲሁም ከፍተኛ አመራሮችና የስፖርት ቤተሰቡ የሚሳተፉበት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በተለይም በጎንደር ከተማ በታሪካዊው የአጼ ፋሲል ቤተ-መንግስት እስከ 100 ሺህ ብር የሚያወጣ የንጉስ እራት መርሃ ግብር ግንቦት 24/2013ዓ.ም. እንደሚካሄድ አስታውቀዋል፡፡
የክለቡን የወደፊት ዘላቂ እድገት ለማምጣት የሚያግዙ የገቢ ምንጮችን በማመቻቸት በኩልም በአዲስ አበባ ፣ ባህር ዳርና ጎንደር ከተሞች ዘመናዊ የገበያ ሞሎችን በሚሰበሰበው ገቢ ለመገንባት መታቀዱንም ጠቅሰዋል፡፡
በጎንደር ከተማ የፋሲል ከነማን የስፖርት አካዳሚን በመገንባት ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት የሚያስችሉ የረጅም ጊዜ እቅዶች መነደፋቸውንም አስራድተዋል።
በኢትዮጵያ የእግር ኳስ ስፖርት ታሪክ ላለፉት 53 ዓመታት ሲንቀሳቀስ የቆየው የፋሲል ከነማ ክለብ የተጫዋቾች ስብጥር ኢትዮጵያዊ አንድነትንና ህብረትን ያጠናከረ እንደሆነም ጠቅሰዋል።
በዘንድሮ የቤት ኪንግ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር ፋሲል ከነማ አሸናፊ መሆኑ ተመልክቷል፡፡
የክለቡ ደጋፊዎች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ሃይለማርያም ፈረደ በበኩላቸው፤ በባህር ዳርና ጎንደር ከተሞች ክለቡን ለመቀበል የሚያስችል መርሃ ግብር መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡
የአቀባበል መርሃ ግብሩ የክልሉ ርዕስ መስተዳድር በተገኙበት ግንቦት 20/2013ዓ.ም. በባህር ዳር ከተማ በማግስቱ ደግሞ በጎንደር ከተማ መስቀል አደባባይ እና በአጼ ፋሲል ስቴዲየም እንደሚከናወን ገልጸዋል።
የአቀባበል መርሃ ግብሩ የኮሮና መከላከያ ፕሮቶኮልን በጠበቀ መንገድ ይካሄዳል፤ የከተሞቹ ስፖርት አፍቃሪዎችና ቤተሰቦች እንዲሁም የክለቡ ደጋፊዎች ተሳታፊ ይሆናሉ ብለዋል፡፡
የፋሲል ከነማ ስፖርት ክለብ ግንቦት 14/213 ዓ.ም. በሃዋሳ ከተማ በሚካሄደው የዘንድሮ የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር ዋንጫውን በማንሳት እንደሚረከብ ይጠበቃል፡፡