ቀጥታ፡

የዘንድሮው ምርጫ የድምጽ መስጫ ቀን ሰኔ 14 መሆኑን የኢትዮጵያ ብሃራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ

አዲስ አበባ ግንቦት 12/2013 (ኢዜአ) የስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ የድምጽ መስጫ ቀን ሰኔ 14 መሆኑን የኢትዮጵያ ብሃራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።

የቦርዱ ኮሙዩኒኬሽን አማካሪ ሶሊያና ሽመልስ በሰጡት መግለጫ  ምርጫው ሙሉ ለሙሉ የመራጮች ምዝገባ በተካሄደባቸው አካባቢዎች ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ይካሄዳል።

የመራጮችም ዝገባ ያልተከናወነባቸው፣ አቤቱታ የቀረበባቸውና ቦርዱ የምዝገባ ሂደቱ ወጥነት ይጎድለዋላል ባላቸው አካባቢዎች ውሳኔ የሚሹ በመሆናቸው በተጠቀሰው ቀን እንምደማይካሄድ ገልጸዋል።

ከነዚህ መካከል በሱማሌ ክልል አቤቱታ የቀረበባቸው 7 ምርጫ ክልሎች፣ ሀረሪ ክልል፤ መተከል ዞንና ሌሎች የጸጥታ ችግር ያለባቸው አካባቢዎች በተጠቀሰው ቀን የማይካሄድ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በተመሳሳይ የደቡብ ምዕራብ ክልል ህዝብ ውሳኔ ብሔራዊ ምርጫው በሚካሄድበት ቀን የሚካሄድ መሆኑን ገልጸዋል።

የድምጽ መስጫ ቀን የተራዘመው በእለቱ የሚያስፈልጉ የምርጫ አስፈጻሚዎችን ለመመልመልና ስልጠና ለመስጠት እንዲሁም ለድምጽ መስጫ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን ለመላክ መሆኑን አውስተዋል።

ለድምጽ መስጫ ቀን የሚያገለግሉ ቁሳቁሶችንም በተሻለ መልኩ ለማጓጓዝ የትራስፖርት እቅድ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

ለድምጽ መስጫ እለት የሚያገለግሉ የህትመት ስራዎችም በቀጣዮቹ አስር ቀናት እንደሚጠናቀቅ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም