ቀጥታ፡

በሲኖዶሶች የተፈጠረው አንድነት ለለውጥ ሂደቱ የጎላ ሚና አለው - የሃይማኖት አባቶች

ባህር ዳር ሀምሌ 26/2010 በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሲኖዶሶች መካከል የተፈጠረው አንድነት በሃገሪቱ የተጀመረው የለውጥ ሂደት ግቡን እንዲመታ የጎላ ሚና እንዳለው በባህርዳር ከተማ የሚገኙ የሃይማኖት አባቶች ተናገሩ። የባህርዳር ሀገረ ስብከት ዋና ፀሐፊ መላከ ብርሃን ፍስሃ ጥላሁን ለኢዜአ እንደገለጹት በታሪክ አጋጣሚ በተፈጠረ አለመግባባት የሀገር ውስጥና የውጭ ሲኖዶስ በመባል ለሁለት ተከፍሎ ላለፉት 27 ዓመት መቆየቱ ህዝበ ክርስቲያኑን ያሳዘነ ተግባር ነበር። በዚህም የአንዲት ጥንታዊት ቤተክርስቲያን የእምነት አባቶች ብቻ ሳይሆኑ ምዕመናኑን በሁለት ጎራ ተከፍሎ በባለአንጣነት ሲተያዩ መቆየቱን ገልፀዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒትር ዶክተር አቢይ አህመድ በሀገሪቱ ዕርቀ ሰላም እንዲወርድና መግባባት እንዲፈጠር ያደረጉት ብርቱ ጥረት በአጭር ጊዜ ተሳክቶ ተለያይተው የኖሩ ሁለቱ ሲኖዶሶች ወደ አንድ እንዲመጡ አስችሏቸዋል። ''በሲኖዶሱ በተፈጠረው እርቀ ሰላምና አንድነትም በሃገሪቱ የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ ግቡን እንዲመታ ያግዛል'' ብለዋል። የጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደመር ብለው ይዘው የተነሱት ፍልስፍና በሀገሪቱ ትልቅ ለውጥ እያመጣ በመሆኑ በርትተው እንዲሰሩ ከጎናቸው ልንቆም ይገባል ብለዋል። የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ ሰይድ መሀመድ በበኩላቸው ተለያይተው የኖሩት ሁለቱ ሲኖዶሶች በተደረገው እርቀ ሰላም አንድ መሆናቸው እኛንም በጣም አስደስቶናል ብለዋል። የሲኖዶሶቹ ወደ አንድ መምጣት በእስልምና ሃይማኖት በኩል ያለውን ልዩነትም በአጭር ጊዜ ወደ አንድ በማምጣት እልባት እንዲያገኝ ፈር ቀዳጅና ምሳሌ ሊሆን የሚችል ተግባር ነው ብለዋል። የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤትም በመካከሉ ያለውን ልዩነት እንዲፈታ ዘጠኝ አባላት ያለው አጥኚ ኮሚቴ ተቋቁሞ ችግሩን ለመቅረፍ ወደስራ ገብቷል። “በዚህም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እንደአርአያ ተጠቃሽ ሆና እኛም ከዚህ ልምድና ተሞክሮ ወስደን በዕርቅ ለመፍታት ትልቅ ተስፋ ይሆነናል” ብለዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የቤተ ክርስቲያኒቱን መለያየት አፍርሰው አንድነት እንዲኖር የማይተካ ሚና ተጫውተዋል ያሉት ደግሞ የሽምብጥ ቅዱስ ሚካኤል ገዳም ዋና መጋቢ ቆሞስ አባ ገብረ ስላሴ ዮሃንስ ናቸው። ይህም ምዕመናንን ያስደሰተና አንድ ያደረገ ቤተክርስቲያኒቱም ዳግም የተወለደችበትና ለረጅም አመታት አጥተነው የቆየነው ሰላም የተመለሰበት የልደት ቀናችን ነው ብለዋል። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የባህርዳር ፈለገ ገነት ካቴድራል ሰበካ ጉባኤ ምክትል ሰብሰቢ አቶ ፋሲል ታየ በበኩላቸው ቤተክርስቲያኗ ታላቅነቷን በማይመጥን ሁኔታ በሁለት ሲኖዶስ ተከፍላ ለዓመታት ቆይታለች። ይህም ቤተክርስቲያኗን ብቻ ሳይሆን የዕምነቱን ተከታዮችና ከዕምነቱ ውጭ የሚገኙ አባቶችና ምዕመናንንም ሳይቀር ሲያሳዝን የቆየ ቢሆንም ያ መከፋፈል አሁን በበሳሉ መሪ ተቋጭቷል ብለዋል። የሰላም ስራ የዚህች ቤተክርስቲያን ድርሻ ብቻ ሳይሆን ከሌሎች ቤተ ዕምነቶች ጋር በጋራ ለምትሰራው ስራም ትልቅ አቅም እንደሚሆናትም አመልክተዋል። የሁለቱ ሲኖዶሶች አንድ መሆን ትልቅ በዓል እንዳከበርን ሁሉ በቅርቡም በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት መካከል ያለውን ልዩነት አጥፍተው ለዚህች ሀገር ሌላ ትልቅ ደስታ እንደሚፈጥሩ እምነታቸው መሆኑንም አስረድተዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም