የኢትዮጵያን ሉአላዊነት ለመፈታተን ከውስጥም ሆነ ከውጭ የሚመጣን ሃይል በጋራ የመመከት ግዴታ አለብን... የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ሉአላዊነት ለመፈታተን ከውስጥም ሆነ ከውጭ የሚመጣን ሃይል በጋራ የመመከት ግዴታ አለብን... የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 12/2013(ኢዜአ) የኢትዮጵያን ሉአላዊነት ለመፈታተን ከውስጥም ሆነ ከውጭ የሚመጣን ማንኛውንም ሃይል በጋራ የመመከት ሀገራዊ ግዴታ አለብን ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ተናገሩ።
ኢትዮጵያ ስድስተኛውን ጠቅላላ ምርጫ ለማካሄድ በዝግጅት ላይ ብትሆንም ምርጫው እንዲደናቀፍና እንዳይካሄድ የሚጥሩ ሃይሎች መኖራቸውንም ይገለፃል።
በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ግጭትና ብጥብጥ በማስነሳት ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር በውስጥም በውጭም የሚንቀሳቀሱ ሃይሎች እንዳሉም በተለያዩ ጊዜ ይጠቀሳል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የብልፅግና፣ የኢሶዴፓ እና የእናት ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች እንዳሉት የፖለቲካ ፓረቲዎች የፖሊሲ ልዩነት ቢኖራቸውም በሀገር ህልውና ና የህዝቦች አንድነት ላይ ግን የጋራ አቋም ሊኖራቸው ይገባል።
ለዚህም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የፖሊሲ ልዩነቶቻቸው አንደተጠበቀ ሆኖ በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ተቀራርበው በጋራ መስራት እንዳለባቸው የጠቀሱት አመራሮቹ፤ በተለይ አሁን ኢትዮጵያን ከገጠሟት ወቅታዊ ሁኔታዎች አንፃር ከየትኛውም ጊዜ በላይ መቀራረብንና በጋራ መቆምን ይጠይቃል ነው ያሉት።
በብልጽግና ፓርቲ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ሃላፊ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ እንዳሉት፣ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ጸንታ እንዳትቆም የሩቅና የቅርብ ጠላቶች ሌት ተቀን እየሰሩ ይገኛሉ።
እነዚህን ጠላቶች ለመመከት የፖለቲካ ፓርቲዎች ምንም ያህል የሃሳብ ልዩነቶች ቢኖራቸውም የኢትዮጵያ ህልውና ጉዳይ አንድ ሊያደርጋቸው እንደሚገባም ገልጸዋል።
"ፓርቲዎች የመመስረታችን ዋና አላማ የሀገር እና ህዝብ ጉዳይ በመሆኑ የኢትዮጵያ ጠላቶች ውጥናቸው እንዳይሳካላቸው በጋራ መቆምና መመከት ይገባል" ብለዋል ዶክተር ቢቂላ።
የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) ሊቀመንበር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በበኩላቸው "ኢትዮጵያዊያን ጠላት ሲመጣ በታሪካችን ተነጣጥለን አናውቅም" ብለዋል።
''ለጠላቶቻችን እድሚያስቡት በቀላሉ የምንፈረከረክ ህዝቦች እንዳልሆን አስረግጠን እናስረዳለን'' ያሉት ፕሮፌሰር በየነ '’ምርጫ እናካሄዳለን ብለናል ያንን የሚያስቆም ሃይል አይኖርም’’ ብለዋል።
ሃላፊነት በጎደለው መልኩ የሚንቀሳቀሱ አንዳንድ አካላትን በጋራ ቆመን ዋጋ ማሳጣት ይኖርብናል በማለትም ጠቅሰዋል።
የእናት ፓርቲ ዋና ጸሃፊ አቶ ጌትነት ወርቁ በበኩላቸው ፓርቲዎች የተለያየ ፖለቲካዊ አመለካከት ቢኖራቸውም በሀገር አንድነትና ሉአላዊነት ላይ የተለየ አቋምና ድርድር መኖር የለበትም ብለዋል።
ፓርቲዎች በጥቃቅን ጉዳዮች ላይ እየተደነቃቀፉ የሚወድቁ ሳይሆኑ በድርድርና ሃብን በጋራ በማንሸራሸር መስራት እንዳለባቸውም ነው የገነጹት።
በጋራ፣ ለጋራ ተጠቃሚነት በመስራት አገርን ማሻገር ይገባል ያሉት የፓርቲዎቹ አመራሮች አገራዊ አንድነትን በሚገነቡ ጉዳዮች ላይ በቀጣይም ልንነጋግርና ልንቀራረብ ይገባል ብለዋል።