መገናኛ ብዙኃን ስለ ሰላም አብሮነት እና የሀገር ግንባታ በትኩረት መሥራት አለባቸው-- የሰላም ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል - ኢዜአ አማርኛ
መገናኛ ብዙኃን ስለ ሰላም አብሮነት እና የሀገር ግንባታ በትኩረት መሥራት አለባቸው-- የሰላም ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል
ግንቦት 12/2013 (ኢዜአ) መገናኛ ብዙኃን ስለ ሰላም አብሮነት እና የሀገር ግንባታ ሥራዎች ላይ በትኩረት መሥራት አለባቸው ሲሉ የሰላም ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን "መገናኛ ብዙኃን ለአብሮነት እና አገር ግንባታ" በሚል መሪ ሐሳብ ውይይት እያካሄደ ነው።
በውይይቱ የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል፣ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር መሐመድ እድሪስ፣ የመገናኛ ብዙኃን ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች እንዲሁም የሀገር ሽማግሌዎችና የኃይማኖት አባቶች ተሳትፈዋል።
በዚሁ ወቅት የሰላም ሚኒስትሯ ሙፈርሃት ካሚል፤ መገናኛ ብዙኃን አንድነትን በሚያጠናክሩና ሰላምን በሚያሰፍኑ ሥራዎች ላይ በትኩረት ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።
መገናኛ ብዙኃንን በአግባቡ አለመጠቀም አገርን እስከ ማፍረስ ሊደርስ የሚችል አደጋ እንደሚያመጣም ጠቁመዋል።
መገናኛ ብዙኃን ለአገር ግንባታ እና ሰላምን ለማስፈን ትልቅ ኃይል አላቸው ያሉት ሚኒስትሯ በሥራቸው እውነትን እና የሀገር ክብርን ማስቀደም አለባቸው ብለዋል።
ከዚህ በተቃራኒ የተለያዩ የፖለቲካ እና የቡድን ፍላጎትን የሚያራምዱ መገናኛ ብዙኃን እንዳሉም ጠቁመዋል።
ከህብረተሰቡ ፍላጎት እና ጥቅም በተቃራኒ በመቆም ህዝብን በማጋጨት አገር ለማፍረስ የሚሰሩ አንዳንድ የመገናኛ ብዙኃን ቆም ብለው ራሳቸውን ማየት እንዳለባቸው ገልጸዋል ።
አሁን ባለንበት ወቅት አገራዊ አንድነት እና ህዝብን የሚያቀራርቡ ሥራዎችን በስፋት እንዲሰሩም ጠይቀዋል።