የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት ዙሪያ የሰጡት አስተያየት የኢትዮጵያን አቋም የሚደግፍ ነው... አምባሳደር ዲና ሙፍቲ - ኢዜአ አማርኛ
የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት ዙሪያ የሰጡት አስተያየት የኢትዮጵያን አቋም የሚደግፍ ነው... አምባሳደር ዲና ሙፍቲ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 12/2013(ኢዜአ) የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌትን በተመለከተ ሰሞኑን የሰጡት አስተያየት የኢትዮጵያን አቋም ያንፀባረቀ አስተያየት መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገለጹ።
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና በሳምንታዊ መግለጫቸው አበይት የሆኑ የዲፕሎማሲ፣ ምጣኔ ሀብታዊ፣ ፖለቲካዊና ዜጋ ተኮር ክንውኖችን አብራርተዋል።
"የአቋም መለዋወጥ የዲፕሎማሲ ባሕሪ ነው" ያሉት አምባሳደር ዲና የአገራት አቋም መለዋወጥም ከዚህ ከዲፕሎማሲ ፖለቲካ ጋር የሚያያዝ ችግር እንደሆነ ገልፀዋል።
ግብፅም በህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት ዙሪያ ቀደም ሲል ታራምድ የነበረውን አቋም በመቀየር ኢትዮጵያ የምታራምደውን አቋም ወደሚደግፍ ሃሳብ መሸጋገሯን ጠቅሰዋል።
ሁለተኛው ዙር የህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት የግብፅ ፍላጎት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አንደማይኖረው ሰሞኑን የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜህ ሹክሪ መግለፃቸው የኢትዮጵያን አቋም ያንፀባረቀ ጥሩ አስተያየት መሆኑንም አምባሳደር ዲና ገልጸዋል።
የሚኒስትሩ ሀሳብ የግድቡ ውሃ ሙሌት የታችኞቹን ተፋሰስ ሀገራት የማይጎዳ መሆኑን የሚደግፍ ሃቅ በመሆኑ በ6 ዙር የሚከናወኑት ቀጣይ ሙሌቶችም የማይጎዳ ስለመሆኑ ያረጋገጠ አስተያየት ነው ብለዋል።
"ግብፅና ኢትዮጵያ የናይል ቤተሰቦች በመሆናቸው የትብብር እንጂ የመናቆር ግንኙነት እንዳይኖር ኢትዮጵያ ፅኑ አቋም አላት" ብለዋል።
ኢትዮጵያ የልማት እንጂ ማንንም የመጉዳት ዓላማ እና ፍላጎት እንደሌላትም የገለጹት አምባሳደር ዲና፤ በዚህ ዙሪያ የአሜሪካ መንግስት የመግለጫ መለዋወጥ፣ ዕውነትነትን ያለማመን ቢሆንም ግድቡን አትሞላም የሚል አቋም ግን እንደሌለ ተናግረዋል።
በፖለቲካው መስክ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በዩጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩሮ ሞሶቨኒ በዓለ ሲመት ተገኝተው ከተለያዩ አገሪት መሪዎች ጋር መወያያታቸውንም አንስተዋል።
ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ከፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን፣ ሱዳንና ግብፅን ጨምሮ ከሌሎች አገራት መሪዎች ጋር በሁለትዮሽና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ፍሬያማ ውይይት አድርገዋል ብለዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኃላፊ ጋር መምከራቸውንም በማንሳት፤ በውይይቱ ወቅት ለኢትዮጵያ እርዳታ ለማቅረብ ፍላጎት እንዳለ የቀይ መስቀል ኃላፊ እንደገለጹላቸው አምባሳደር ዲና ጠቅሰዋል።።
ከሰላም ሚኒስትር ጋር በተዘጋጀ የቪድዮ ኮንፈረስ ላይ ኢትዮጵያ ሁለገብ ለውጥና የተቀናጀ ብልፅግና ለማምጣት ያላትን ፍላጎት ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ገለፃ ማድረጋቸውንም ጠቁመዋል።
ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ምክር ቤት ፅሕፈት ቤት ጋር በመተባበር በግድቡ ጉዳይ ከፖለቲካ ፓርቲዎችና ከሲቪክ ማህበራትና ሐይማኖት ተቋማት ተወካዮች ጋር ውይይት መደረጉንም ነው አምባሳደሩ በመግለጫቸው የገለጹት።
በዋሽንግተን የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን በኢትዮጵያ ላይ የሚደርገውን ዓለም አቀፍ ጫና አና ጣልቃ ገብነት በሰልፍ የኮነኑበት፣ በካናዳና ጀርመን ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያዊያን ለግድቡ ድጋፍ ያደረጉበት ሳምንት ነበር ብለዋል።
በዚህም በአሜሪካ መንግስት በተሰጠው የጣልቃ ገብነት መግለጫ ላይ የኢትዮጵያ ጠንካራ ግብረ መልስ የታየበት ነበር ብለዋል።
በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ረገድም የቱሪዝም ዘርፍን ለማጠናከር ስትሪንግ ኮሚቴ የተቋቋመበት፣ በፋርማሲ ዘርፍ ለመሰማራት የፈለገ የውጭ ኩባንያ በኢትዮጵያ ቅድመ ጥናት አድርጎ የተመለሰበትና በስፔይን የኢትዮጵያን ቡና የማስተዋወቅ ሁነትን ለአብነት አንስተዋል።
በተመለከተ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ የአፍሪካ ሕብረት፣ አሜሪካና እንግሊዝን ጨምሮ የተለያዩ አገራት 6ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ለመታዘብ ፍላጎታቸውን መግለፃቸውን ጠቅሰዋል።
የተለያዩ 36 አገራዊ ተቋማት ደግሞ ምርጫውን ለመታዘብ መዘጋጀታቸውን አምባሳደር ዲና ገልፀዋል።