የ 2013 ምርጫና ሰላም

86

በዳግም መርሻ (ኢዜአ)

ዜጎች በጉጉት የሚጠብቁት ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ለዴሞክራሲ ስርአት መሰረት ይጣልበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ይሁንና ከመራጮች ምዝገባና ከድምጽ መስጫ ካርድ ዝግጅት መዘግየት ጋር ተያይዞ ምርጫው ከሁለትና እስከ ሶስት ሳምንታት ሊገፋ እንደሚችል፣ አብሮም የአዲስ አበባና የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤቶች ምርጫ ከሀገር አቀፉ ምርጫ ጋር በተመሳሳይ ቀን እንዲካሄድ  መወሰኑን የምርጫ ቦርድ አሳውቆ በዚሁ መልኩ እየተሰራ ይገኛል፡፡

ቦርዱ በየጊዜው የሚሰጣቸው መግለጫዎች እንደሚያመለክቱት በምርጫው የሚሳተፉ እጩዎችና የመራጮች ምዝገባ ተጠናቋል።

በምርጫው የሚሳተፉ ፓርቲዎችና የግል ተወዳዳሪዎች የምረጡኝ ቅስቀሳና ክርክር ከየካቲት 8 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ እየተካሄደ ነው። በመራጭነት ይመዘገባሉ ተብሎ ከተገመተው 50 ሚሊዮን ሕዝብ ውስጥ እስካሁን ወደ 36 ነጥብ 2 ሚሊዮን መራጮች እንደተመዘገቡ የቦርዱ ሪፖርት ያመላክታል።

የምርጫ ደህንነትና ሰላም ለምርጫው ፍትሀዊነት፣ ተአማኒነት፣ አሳታፊነት እና በአጠቃላይ ለምርጫው ስኬት ጉልህ ድርሻ አለው። ምክንያቱም ምርጫ ደህንነቱ የተጠበቀና ሰላማዊ ካልሆነ የዲሞክራሲያ መስፈርቶችን አያሟላም።

ምርጫ ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ወሳኝ ቢሆንም በራሱ ይዞ የሚመጣቸው ስጋቶች አሉ።  ለዚህም ከዚህ በፊት በአፍሪካ፣ በኤሲያና በላቲን አሜሪካ ሀገሮች ከምርጫ ጋር ተያይዞ የተከሰቱ በርካታ ቀውሶችን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል።

ወደ አህጉራችን አፍሪካ ስንመጣ እ.አ.አ ታህሳስ 2007 በጎረቤታችን ኬንያ ከተደረገው ምርጫ በኋላ በተፈጠረው ሁከትና ብጥብጥ ከአንድ ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰዎች ህይወታቸውን ሲያጡ ከ500 ሺህ በላይ የሚሆኑት ደግሞ ከመኖሪያ ቀዬአቸው እንዲፈናቀሉ ምክንያት ሆኗል። ይህ ደግሞ በኬንያ እስካሁንም ድረስ ምርጫ በመጣ ቁጥር በዜጎች ላይ ስጋት እንዲፈጠር ያደረገ ክስተት ሆኖ ተመዝግቧል።

በኢትዮጵያም ምርጫው ለግጭት መነሾ ሊሆን ይችላል ብለው የሚሰጉ ዜጎች ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም። ለዚህ ደግሞ በ1997 ዓ.ም ከተካሄደው ሀገራዊ ምርጫ ጋር ተያይዞ በወቅቱ የተከሰተው ሁኔታ ለስጋቱ እንደ ማጠናከሪያ ሀሳብ ተደርጎ ይጠቀሳል። 

በዘመናዊ የኢትዮጵያ ታሪክ የ1997 ዓ.ም ምርጫ በብዙ መልኩ ታረካዊ ነበር ቢባል ማጋነን አይሆንም። ይህ ምርጫ በተፎካካሪ ፓርቲዎች መካከል የጋለ ፉክክር የታየበት ከመሆኑም ባሻገር በበርካታ ዜጎች ዘንድ ለአጭር ጊዜም ቢሆን ተስፋን ፈንጥቆ ያለፈ ምርጫ ነው። ይሁን እንጂ በምርጫው ማግስት በተነሳው ውዝግብና ብጥብጥ ምክንያት በርካታ ንጹሀን ህይወታቸውን ያጡበትና በርካቶችም ለእስር የተዳረጉበት ክስተት ነበር። ይህም ምርጫው መጥፎ ጠባሳ ጥሎ እንዲያልፍ አድርጓል።

በዚህም ሳይወሰን ከ1997 ምርጫ ወዲህ የተካሄዱት ምርጫዎች በፖለቲካ ምህዳሩ መጥበብ ምክንያት ነጻና ፍትሀዊ ያልነበሩ ከመሆኑም በዘለለ ህዝቡም ከፍርሀት ቆፈንና ያልተላቀቀበት ሁኔታ እንደነበር ይታወሳል።

ይህ የሚያሳየው እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የዲሞክራሲ ባህል ባልዳበረባቸው ሀገሮች ከምርጫ ጋር የተያያዙ አለመግባባቶችና ግጭቶች የመከሰታቸው አጋጣሚ እንግዳ እንዳልሆነ ነው። ይህን በዘርፉ የተደረጉ ጥናቶችም ያረጋግጣሉ።

ከምርጫ ጋር የተያያዙ ግጭቶች እንኳን ዲሞክራሲ ስር ባልሰደደባቸው ሀገራት ይቅርና የዲሞክራሲ ቁንጮና ተምሳሌት ተብለው በሚጠሩ ሀገራትም ሊከሰት እንደሚችል እ.አ.አ በ2020 በአሜሪካ የተካሄደው ምርጫ ጥሩ ምሳሌ ነው። በዚህ ምርጫ በወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንትና የሪፓብሊካን ፓርቲ ወክለው በምርጫው የተወዳደሩት ፕሬዝዳንት ትራምፕ እና ደጋፊዎቻቸው ምርጫው ከፍተኛ ማጭበርበር የተሞላበት ነው ብለው ባቀረቡት ክስ ምክንያት ባልተለደ ሁኔታ ለረጅም ወራቶች የዘለቀ ውዝግብና ግጭት ሊከሰት ችሏል።  ከዚህ መረዳት የሚቻለው ነገር ቢኖር ምርጫ አብዛኛውን ጊዜ ከእንከን የጸዳ ወይም ፍጹም ነው ብሎ መደምደም እንደማይቻል ነው።

የምርጫ ደህንነትና ሰላም በምርጫ ወቅት ሲታሰብ አንድን ምርጫ ደህንነቱ የተጠበቀና ሰላማዊ እንዳይሆን የሚያደርጉ ሁኔታዎች እንዳሉ ይታወቃል።

ከምርጫ ጋር የተያያዙ የግጭት መነሻዎችን በሚመለከት ወርልድ ቪዥን የተሰኘው አለም አቀፍ በጎ አድራጎት ድርጅት ባልደረባና በአሁኑ ወቅት በሰላም ዙሪያ በደቡብ ሱዳን  ሙያዊ አገልግሎት እየሰጡ ያሉት አቶ ብሩክ ከበደ ከፕራይም ሚዲያ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ እንደገለጹት ከምርጫ ጋር በተያያዘ ሰላም ሊደፈርስ የሚችልበትን የተለያዩ ምክንያቶች ይዘረዝራሉ።

እርሳቸው እንደሚሉት በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ፓርቲዎችና እጩዎች ለደጋፊዎቻቸው  የሚያስተላልፉት ስሜት ቀስቃሽ ንግግርና ከእውነት የራቀ ፖለቲካዊ ትርክት አንደኛው የግጭት መንስኤ ሊሆን ይችላል። በተለይም የፖለቲካው አሰላለፍና አደረጃጀት ከማንነትና ከጎሳ ጋር ትስስር ካለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ያለውን ልዩነት መሰረት አድርገው  ደጋፊዎቻቸውን በመቀስቀስና ስሜት ውስጥ እንዲገቡ በማድረግ ውጥረት እንዲፈጠርና ሁኔታው ወደ ደም አፋሳሽ ግጭት እንዲያመራ ምክንያት ሊሆኑ እንደሚችሉ ያስገነዝባሉ።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ አንዳንድ ፓርቲዎች ማሸነፍን ብቻ እንደ ግብ አድርገው ወደ ምርጫ ከገቡ የምርጫው ውጤት ካሰቡት ውጪ ሆኖ ሲገኝና ውጤቱን በጸጋ ለመቀበል ዝግጁ ካልሆኑ ሁኔታው ወደ ጭቅጭቅና መካረር ተለውጦ ግጭት ይወልዳል።

እንደ አቶ ብሩክ አነጋገር በምርጫ ወቅት የሚከሰቱ ግጭቶችና የህግ የበላይነት አለመከበር ዜጎች በመንግስት እምነት በማጣት  ለውጭ  ጣልቃ ገብነቶችና በር ይከፍታሉ፡፡

የምርጫን ደህንነትና ሰላማዊነት ከሚያስተጓጉሉት ጉዳዮች መካከል ሌላው ተጠቃሽ ጉዳይ በተለያዩ ምክንያቶች በምርጫው እንዳይሳተፉ የተደረጉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ደጋፊዎችና ሌሎችም ምርጫው እንዳይካሄድ የማይፈልጉ አካላት ሊፈጠሩ የሚችሉት የግጭት ሴራ ነው።

በተጨማሪም የምርጫ አስፈጻሚ አካላት ነጻ፣ ገለልተኛ እና ግልጽነት የጎደለው አሰራር  አለው ተብሎ የሚታመን ከሆነና በህዝብና በፖለቲካ ፓርቲዎች እምነት የማይጣልበት ተቋም ከሆነ ይህ በህብረተሰቡ ዘንድ ቅሬታ ፈጥሮ በቅድመ ምርጫና በድህረ ምርጫ ወቅት የውዝግብ መንስኤ የመሆን እድሉ ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል ያስረዳሉ።

በተመሳሳይም የጸጥታ አስከባሪ አካላት በምርጫው ሂደት ነጻና ገለልተኛ ሆነው ሀላፊነታቸውን ካልተወጡ ለግጭትና ቀውስ ድርሻ ሊኖራቸው እንደሚችል ያነሳሉ።

በመሆኑም ተቀባይነት ያለውና ከችግር የራቀ ምርጫ ለማድረግ የማስፈጸም አቅምና ሙያዊ ብቃት የተላበሰ፣ ግልጽነት ያለው፣ ገለልተኛና ተቋማዊ ነጻነት ኖሮት የሚንቀሳቀስ የህግ አስፈጻሚና የጸጥታ አካል ለምርጫ ስኬት እንደ አንድ ቅድመ ሁኔታ ይቀመጣል። እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች ባልተሟሉበት ሁኔታ ምርጫው ለውዝግብና ግጭት የመዳረግ እድሉ ከፍተኛ ነው።

በርካታ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት የሀገራት የፖለቲካና አስተዳደራዊ ዘይቤ ከምርጫ ጋር ተያይዞ ለሚከሰቱ ግጭቶች አባባሽ ምክንያት ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ የህብረተሰቡን የልማት ተጠቃሚነት ያገለለ፣ ከብቃት ይልቅ ለፖለቲካ ታማኝነት ቅድሚያ የሚሰጥ፣ ሙስናን የሚያበረታታ፣ ለህግ የበላይነት መከበር ቁርጠኝነት የሌለው መንግስት ስልጣኑን በያዘበት ሀገር ውስጥ የሚካሄድ ምርጫ የታፈኑና ድምጾች  እንዲፈነዱ ሊያደርግ እንደሚችሉ ይጠቁማሉ።

ይሀም በምርጫው ሂደት ስልጣን ላይ ካለው የመንግስት አስተዳደር ጋር የተለያየ የጥቅም ትስስር ኖሯቸው አመራሩ በስልጣን እንዲቀጥል በሚፈልጉ እና አመራሩ ከስልጣን እንዲነሳ በሚፈለጉ ሀይሎች መካከል ቅራኔና ክፍፍል ፈጥሮ ወደ ብጥብጥ ሊያመራ አንደሚችል ይገልጻሉ።

ከዚህ በተጨማሪም የምርጫ ታዛቢዎች የተዛባና ሚዛናዊነት የጎደለው መግለጫና ሪፖርት ከምርጫ ጋር ተያይዞ ለሚነሱ ግጭቶች  አስተዋጽኦአቸው የሚናቅ አይደለም።

እንደሚታወቀው አገራችን ባሁኑ ጊዜ በብዙ ፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥ ትገኛለች። በተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ ችግሮችና ሰላምን የሚያደፈርሱ ሁኔታዎች እንዲሁም ከህዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ በግብጽ፣ በሱዳን እና አሜሪካንን ጨምሮ በአንዳንድ ምእራባዊያን ሀገራት እየተደረጉ ያሉት ሀሰተኘ ፕሮፓጋንዳዎችና ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎች በምርጫው ላይ ጥላቸውን እንዳያጠሉ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል።

በምርጫ ወቅት ሊከሰቱ የሚችሉ ግጭቶችን ለማስቀረት ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ትልቅ ሀላፊነት አለባቸው። ለዚህም በምርጫ ቅስቀሳቸው ከግጭት ቀስቃሽ ንግግሮችና ሀሰተኛ ትረካዎች ራሳቸውን መቆጠብ እና ደጋፊዎቻቸው የምርጫውን ውጤት በጸጋ እንዲቀበሉ  ግንዛቤ የመፍጠር አለባቸው።

ከምርጫው መካሄድ ጋር ተያይዞም ግጭት እንዲፈጠር በጉጉት የሚጠብቁ ሀይሎች መኖራቸውን ታሳቢ በማድረግ ሁሉም ፓርዎችና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ለሀገር አንድነት ቅድሚያ እንዲሰጡና ይህንን አስቸጋሪ ጊዜ በጥበብና በማስተዋል ማለፍ እንሚገባቸው  የሰላም አማካረው ያስረዳሉ።

ህብረሰሰቡና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እጅግ ጥንቃቄ የተሞላበት ታሪካዊ ሀላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አቶ ብሩክ ከበደ ሙያዊ ምክራቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም