ቀጥታ፡

የአረንጓዴ አሻራ ከአከባቢ ጥበቃ በተጨማሪ ኢትዮጵያን ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ያደርጋታል- ዓለም አቀፍ ኢንቨስተሮች

ግንቦት 11/2013 (ኢዜአ) የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከአከባቢ ጥበቃ በተጨማሪ ኢትዮጵያን ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ እንደሚያደርጋት በኢትዮጵያ የሚገኙ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ኢንቨስተሮች ገለጹ።

የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂኔር ስለሺ በቀለ የ2013 የአረንጓዴ አሻራን በተመለከተ በኢትዮጵያ ለሚገኙ ዓለም አቀፍ ኢንቨስተሮች ገለጻ አድርገዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ግቦችና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ግንባታ ያላትን ቁርጠኝነትና አጠቃላይ የመርሃ ግብሩን ዓላማ አብራርተዋል።

"ኢትዮጵያን እናልብሳት" በሚል መሪ ሃሳብ በሚተገበረው የ2013 አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር 7 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል መታቀዱን አብራርተዋል።

ከዚህም ውስጥ 1 ቢሊዮን ችግኞች ለጎረቤት ሀገራት የሚቀርብ መሆኑንም ነው ያነሱት።

በገለጻው የተገኙ ኢንቨስተሮችም ኢትዮጵያ ለአረንጓዴ ልማት የሰጠችውን ትኩረት አድንቀዋል።

የአንሞል ኩባንያ ዋና ስራ አስኪያጅ ራጃቭ ኩማር ሻርማ ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት ምቹና ተመራጭ ሀገር መሆኗን ገልጸዋል።

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የኢትዮጵያን ገጽታ እየቀየረ መሆኑን ገልጸው፤ ይህም በርካታ ኢንቨስተሮችን ወደ ኢትዮጵያ የመሳብ እድል ይፈጠራል ብለዋል።

የሞሃን ኩባንያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ማዮር ኮታሪ በበኩላቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ የኩባንያዎች ስኬት የሚመዘነው ለአከባቢ ጥበቃ እያበረከቱ ባለው አስተዋጽኦ እየሆነ መምጣቱን አንስተዋል።

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በኢትዮጵያ ያሉ ኩባንያዎች  ስለ አከባቢ ጥበቃ ከወዲሁ ልምምድ እንዲያደርጉ ያግዛል ብለዋል።

የኩባንያቸው ሰራተኞች በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ንቁ ተሳትፎ ያደርጋሉ ብለዋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ለሊሴ ነሜ፤ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚሰማሩ ኩባንያዎች ለአከባቢ ጥበቃ ትኩርት እንዲሰጡ ክትትል እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎችን ከአረንጓዴ ልማትና አከባቢ ጥበቃዎች ጋር የማስተሳሰር ስራ በመስራት ኩባንያዎች ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጡ እንደሚደረግም ነው ያነሱት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም