የሃይማኖት አባቶችና የሲቪክ ማኅበራት ግድቡን በተመለከተ ኢትዮጵያ ያላትን አቋም ማስተጋባት አለባቸው … ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የሃይማኖት አባቶችና የሲቪክ ማኅበራት ግድቡን በተመለከተ ኢትዮጵያ ያላትን አቋም ማስተጋባት አለባቸው … ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
ግንቦት 11/2013(ኢዜአ) የሃይማኖት አባቶችና የሲቪክ ማኅበራት ተወካዮች የታላቁ ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በተመለከተ የተያዘውን አቋም ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በማሳወቅ ሚናቸውን እንዲወጡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጠየቀ።
ሚኒስቴሩ ከሃይማኖት አባቶችና ከሲቪክ ማኅበራት ተወካዮች ጋር ግድቡን በተመለከተ ዛሬ ውይይት አካሂዷል።
የሚኒስቴሩ የድንበርና ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች አማካሪ አምባሳደር ኢብራሂም ኢድሪስ፤ የታችኛው ተፋሰስ አገሮች ከመርህ ውጪ እየተንቀሳቀሱ ነው ብለዋል።
በተለይም ኢትዮጵያ ያልተሳተፈችበትን የቅኝ ግዛት ውል በማጣቀስ የግድቡን ሥራ ለማስተጓጎል በጋራ እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃም የኢትዮጵያን ፍትሃዊና ምክንያታዊ የውሃ አጠቃቀም መርህ ባላገነዘበ መልኩ ክስና ወቀሳ እያቀረቡ መሆኑንም ነው የጠቆሙት።
ይህንንም ተከትሎ ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለመፍጠርና ኢትዮጵያ የውሃ ቅኝ ግዛት ሰለባ ለማድረግ እየሰሩ መሆናቸውን የተናገሩት አማካሪው፤የሃይማኖት አባቶችና ሲቪክ ማኅበራት ግድቡን በተመለከተ ሕዝቡን በማስገንዘብና በማንቃት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም የኢትዮጵያን አቋም ለዓለም ኅብረተሰብ ማስገንዘብ እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት።
የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት በበኩሉ ኅብረተሰቡ የሚያደርገውን ድጋፍ እንዲያጠናክር አሳስቧል።
በጽህፈት ቤቱ የፐብሊክ ዲፕሎማሲና የዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር ሄኖክ ዓለማየሁ፤ ሕዝቡ ለግድቡ የሚያደርገውን የገንዘብ መዋጮና የቦንድ ግዥ እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።
ግድቡን በተመለከተ ኢትዮጵያ ያላትን የፍትሃዊነትና የምክንያታዊነት የውሃ አጠቃቀም መርህ ለዓለም ኅብረተሰብ ማሳወቅ ይገባልም ብለዋል።
በተጓዳኝም ግድቡ ለታችኛው ተፋሰስ አገሮች ያለውን ጥቅም ለሀገራቱ ህዝቦች ማስረዳት ይገባል ነው ያሉት።
ለዚህም የማኅበራዊ ሚዲያን በመጠቀም የተዛቡ መረጃዎችን ጭምር በማስተካከል የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።