ቀጥታ፡

ህገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችን ድርጊት ለማስቆም ህጋዊ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ ተመለከተ

ባህር ዳር፤ ግንቦት 11/2013 (ኢዜአ) ወጣቶችን ባልተጨበጠ ተስፋ እያባበሉ ለከፋ መከራና እንግልት የሚዳርጉ ህገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችን ድርጊት ለማስቆም በተደራጀ አግባብ ህጋዊ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባ ተመለከተ።

ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ለመከላከል የሚያግዝ የአማራ ክልላዊ የምክክር መድረክ  በላሊበላ ከተማ ተካሄዷል።  

የክልሉ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ደረጀ አበጀ በወቅቱ በተለይ ለኢዜአ እንዳሉት፤  በአማራ ክልል በቀን በአማካኝ 150 ሰዎች በህገ-ወጥ ደላሎች ተታለው  ወደ ውጭ  ለስደት እየተዳረጉ ይገኛል።

በምስራቅ አማራ በባቲ በኩል ጂቡቲ ብሎኝ ሳኡዲ አረቢያ የሚሻገሩ፤  በምዕራብ አማራ በመተማ መስመር ደግሞ ከሌሎች ክልሎች የሚመጡ አብዛኛዎቹ ወጣቶች የሆኑ በህገ-ወጥ መንገድ ከሃገር እየወጡ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ወጣቶቹ በህገ ወጥ  አዘዋዋሪች ያልተጨበጠ ተስፋ እየተታለሉ የገቢ ማስገኛ ስራቸውን ጭምር ጥለው ከፍተኛ ገንዘብ በመክፈል በጉዞ ላይ ለከፋ  ችግር እየተጋለጡ ነው ብለዋል።

እንደ ክልሉ መንግስት በህገ-ወጥ መንገድ ከሃገራቸው የሚወጡ ዜጎችን ሊደርስባቸው የሚችለውን አካላዊና ስነ-ልቦናዊ ጉዳት በማስተማር ለመከላከል ጥረት ቢኖርም የህገ-ወጥ ደላሎች አለማቀፋዊ ትስስር በመጠቀም ስለሚሰሩ ችግሩን ለማስቆም አስቸጋሪ እንዳደረገው አቶ ደረጀ ተናግረዋል።

ችግሩን በመሰረታዊነት ለመከላከል በተቀናጀ አግባብ መስራት እንደሚገባ አመልክተው፤ ፖሊስና አቃቢ ህግም በህገ-ወጥ ደላሎችና አዘዋዋሪዎች ላይ አስተማሪ ህጋዊ እርምጃ በመውሰድ ማስተካከል እንደሚጠበቅባቸው  ገልጸዋል።

በዚህ ወቅት ወደ ውጭ በህገ-ወጥ መንገድ የሚወጡ ሰዎች የሚደርስባቸው አስከፊ ችግር እንዳለ  ሆኖ የኢትዮጵያን ወድቀት የሚሹ የአካባቢው ሀገራት ጠልፈው ላልተገባ  ዓላማ የማዋላቸው አጋጣሚ ሰፊ በመሆኑ ችግሩን ለመከላከል የሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል።

''ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል አዲስ የወጣውን የፌዴራል መንግስት አዋጅ መሰረት በማድረግ የሚመለከታቸው አካላትን ያካተተና በክልሉ ጠቅላይ አቃቢ ህግ የሚመራ የጥምረት አደረጃጀት ተፈጥሮ እየተሰራ ነው'' ያሉት ደግሞ የክልሉ ጠቅላይ አቃቢ ህግ አቶ ገረመው ገብረ ጻድቅ ናቸው።

ቀደም ሲል ክፍተት የነበረባቸውን አሰራሮች ፈትሾ በማሻሻል ህገ-ወጥ ደላላዎችን ለመቆጣጣር እየተሰራ መሆኑን  ገልጸው ሆኖም   ከጉዳዩ ውስብስብነት አንፃር ለውጤታማነቱ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ትኩረት እንደሚያሻው አስረድተዋል።

ጠቅላይ አቃቢ ህግ የጥምረቱ አስተባባሪ እንደ መሆኑ መጠን ተገቢውን ስራ ለማከናወን  እቅዶችን በማዘጋጅት ላይ ነው ብለዋል።

መንግስት ህገ-ወጥ ስደትን ለመከላከል የስራ እድል ፈጠራ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ  የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አየለች እሸቴ ናቸው።

ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ከሃሳብ እስከ ተግባር እንዲሁም ከመነሻ እስከ መዳረሻ የተጠላለፈ ወንጀል በመሆኑ ከውጤቱ ጥሩ ነገር መጠበቅ አይቻልም ብለዋል።

መንግስት ወንጀሉን ለመከላከል ለወጣቱ በሀገሩ  ሰርቶ መለወጥ እንዲችል የስራ እድልን ዓይነተኛ አማራጭ አድርጎ ከመስራት በተጨማሪ በህጋዊ መንገድ ዜጎች ወደ ውጭ  ሂደው የሚሰሩበትን እድል ማመቻቸቱን ገልጸዋል።

ወጣቱ በህገ-ወጥ ደላሎች እየተታለለ በማይጨበጥ የምናብ ተስፋ ለአላስፈላጊ መስዋትነት ከሚዳረግ መንግስት ያመቻቸውን አማራጮች በመጠቀም እራሱን ለለውጥ ማዘጋጀት እንዳለበትም ተናግረዋል።

በአማራ ክልል በበጀት ዓመቱ አንድ ሺህ 434 ሰዎች በህገ ወጥ መንገድ ከሀገር ለመውጣት ሲሞክሩ ተይዘው የምክር አገልግሎት ተሰጥቷቸው ወደየቤተሰቦቻቸው እንዲመለሱ መደረጉም ተወስቷል።

ለሁለት ቀናት በተካሄደው የምክክር መድረክ የፌዴራልና ክልል ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ መስሪያ ቤቶች አመራሮች ፣ የክልሉ ጠቅላይ አቃቢ ህግና ሌሎችም  ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም