ቀጥታ፡

ምርጫውን በነፃ እና በፍትሃዊነት በማካሄድ የዴሞክራሲ ባለቤቶች መሆናችንን ለዓለም ማሳየት አለብን - ዶክተር ጌዲዮን

አዲስ አበባ ግንቦት 11/ 2013 (ኢዜአ) ምርጫውን ነጻ፣ ፍታሃዊ በማድረግ በገለልተኝነት በማካሄድ የዴሞክራሲ ባለቤት እኛው መሆናችንን ለዓለም ማሳየት አለብን ሲሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ ተናገሩ።

በሠላም ሚኒስቴር አዘጋጅነት ሲካሄድ የቆየው "የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሽግግር ሂደት፣ ብሔራዊ መግባባት፣ ምርጫ 2013 እና ከዚያ ባሻገር" አገራዊ የምክክር መድረክ ተጠናቋል።

በማጠቃለያው መድረክ የሠላም ሚኒስትሯ አማካሪ ዶክተር ሞገስ ደምሴ 'ምርጫ 2013 እና ከዚያ ባሻገር'ን የዳሰሰ ሰነድ አቅርበዋል።

በሰነዱ የምርጫ ምንነት፣ አስፈላጊነትና ሂደት እንዲሁም የፖለቲካ ሽግግር ሂደት ምን ይመስላል? የሚሉ ሃሳቦች ለውይይት ቀርበዋል።

በአገሪቱ ውጤታማ ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሽግግር እንዲደረግ መንግስት የመወዳደሪያ አውዱን ያሰፉና ነፃ ምህዳር የፈጠሩ እርምጃዎችን መውሰዱ በሰነዱ ተገልጿል።

ነፃና ገለልተኛ የምርጫ ቦርድ ማቋቋም፣ የሕግ ማዕቀፍ ማዘጋጀት፣ የፍትህ ተቋማት ማሻሻያ ማድረግና የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ማቋቋም ከተወሰዱ እርምጃዎች ተጠቅሰዋል።

በቅድመ ምርጫ የተወሰዱ እርምጃዎች ለሚደረገው ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ጠቃሚ መሆናቸውንም አንስተዋል።

እንደ ዶክተር ሞገስ ገለፃ 6ኛውን አገራዊ ምርጫ በስኬት ማጠናቀቅ ከተቻለ ለዴሞክራሲ መከፈትና ለተጀመረው የፖለቲካ ሽግግር መሰረት ይሆናል።

"እውነተኛ እና ቀጣይነት ያለው የፖለቲካ ምክክር ማድረግ ዋልታ ረገጥ አስተሳስብን ለማክሰምና አንድነትን ለማጠናከር አንድምታም ይኖረዋል" ብለዋል።

ለሀገረ መንግስት አወቃቀርና ውስጣዊ አሰራር አቅም ሊፈጥር እንደሚችልም ዶክተር ሞገስ አንስተዋል።

የፈረዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ በበኩላቸው፤ ምርጫው ውጤታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ  በቅድመ ምርጫ የሚከናወኑ ተግባራት ወሳኝ ናቸው ይላሉ።

በተለይ የሕግ ማዕቀፍ ማዘጋጀት የምርጫውን ሂደት ዴሞክራሲያዊ ያደርገዋል ብለዋል።

"ከዚህ ቀደም በተካሄዱ ምርጫዎች በአስፈፃሚዎችና በሕግ ላይ የሚኑሱ ቅሬታዎችና ስሞታዎች በዘንድሮው ምርጫ እንዳይደገሙ የተሰራው ስራ 6ኛውን አገራዊ ምርጫ ለየት ያደርገዋል" ነው ያሉት።

እንደ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ ገለጻ ምርጫ ቦርድ ነፃና ገለልተኛ ሆኖ እንዲቋቋም መደረጉ፣ የሲቪክ ማህበራትና ሚዲያዎች ነፃ ሆነው መንቀሳቀሳቸው በቅድመ ምርጫ የተሰሩ ስራዎች ናቸው።

መንግስት የምርጫ አስፈፃሚዎች ነፃ፣ ገለልተኛና ጠንካራ እንዲሆኑ ማድረጉ ያለውን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይም አንስተዋል።

"የዴሞክራሲ ባሕላችን ገና በመሆኑ በሂደቱ የተለያዩ ተግዳሮቶች ሊያጋጥሙ ይችላሉ" ያሉት ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ፤ በቀጣይ እየተስተካከለ እንደሚሄድ ጠቁመዋል።

6ኛውን አገራዊ ምርጫ ነፃ፣ ፍትሃዊና በገለልተኛነት የሚጠናቀቅ ማድረግ ከተቻለ የዴሞክራሲው ባለቤት እኛው እንሆናለን ብዬ አስባለሁ" ብለዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ ምሁር ፕሮፌሰር ካሳሁን ብርሃኑ በበኩላቸው የዘንድሮው ምርጫ የተሻለና ውጤታማ ሆኖ ይጠናቀቃል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።

"ዴሞክራሲ፣ ምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የብሄሮች መብት አገር ለማፅናት ጠቃሚ ነገሮች ናቸው" ያሉት ፕሮፌሰሩ ይሁን እንጂ እነዚህ በየራሳቸው አገርን የሚተኩ አይደሉም ብለዋል።

በምርጫ የተሻለ የመንግስት አደረጃጀት ለማቋቋምና ብሔራዊ መግባባት የሚያመጡ ምክክሮች የሚያካሂድ መንግስት ሊመሰረት እንደሚችል እምነታቸውን ገልጸዋል።

በሠላም ሚኒስቴር አዘጋጅነት ለሦስት ቀናት የተካሄደው የምክክር መድረክ ዛሬ ተጠናቋል።

በመድረኩ ከሕዝቡ የቀረቡ ጥያቄዎችን ጨምሮ ኢትዮጵያን በሽግግር ጎዳና፣ የሽግግር ተሞክሮዎች ንጽጽራዊ ትንታኔ፣ ጉዞ ወደ ብሔራዊ መግባባት፣ ተግዳሮቶችና መፃኢ እድሎች እንዲሁም ምርጫ 2013ን የሚዳስሱ የምክክር መነሻ ሀሳቦች ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም