በኢትዮጵያ ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮችን በድል ለመወጣት እንደ እግር ኳስ የሕብረት ሥራ ያስፈልጋል - አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮችን በድል ለመወጣት እንደ እግር ኳስ የሕብረት ሥራ ያስፈልጋል - አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 11/2013 (ኢዜአ)በኢትዮጵያ ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮችን በድል ለመወጣት እንደ እግር ኳስ የሕብረት ሥራ ያስፈልጋል ሲሉ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ተናገሩ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እግር ኳስ አሰልጣኝ የነበሩት ሰውነት ቢሻው "እግር ኳስ የአንድነት ምልክት ነው" ይላሉ።
ለዚህ አባባላቸው የኢትዮጵያ ሕዝብ ብሔራዊ የአንድነት ስሜት ቡድኑ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ባለፈበት በ2006 ዓ.ም የተሰጠውን የማይረሱትን ክስተት ያስታውሳሉ።
ኢትዮጵያ ሕዝብ አንድ ሕዝብ ነው የሚሉት አሰልጣኝ ሰውነት፤ አሁን የሚስተዋሉ ልዩነቶችና አለመግባባቶች የሕዝብ ችግሮች እንዳልሆኑ እምነታቸውን ገልጸዋል።
እነዚህ የሠላም እጦት ችግሮች ተፈተው የቀደመ ጠንካራ አብሮነት እንደሚመጣ፣ ጠንካራ ኢትዮጵያም እንደምትፈጠርም ያምናሉ።
አገሪቱ የሚያጋጥሟት ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች የአንድ አካባቢ ብቻ ሳይሆኑ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን የሠላም ችግሮች እንደሆኑ ገልጸው በድል ለመወጣት ትብብር ያስፈልጋል ብለዋል።
በእግር ኳስ ድል ለማድረግ የሁሉም ተጫዋቾች የቡድን ሥራ እንደሚያስፈልግ የሚገልጹት አሰልጣኝ ሰውነት፤ የሠላም ጉዳይም የሁሉንም ትብብር ይጠይቃል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ላይ የተጋረጡ ችግሮችን በድል ለመወጣትና ወደ ሠላም ለመምጣትም እንደ እግር ኳሱ ሁሉ ኢትዮጵያዊያን በሕብረት መቆማቸው አማራጭ የሌለው ጉዳይ እንደሆነም ተናግረዋል።