ቀጥታ፡

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታ ሙሉ በሙሉ ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 11/2013(ኢዜአ) 650 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኃይል ማስተላለፊያ መሥመር ዝርጋታ ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁ ተገለጸ።

የኃይል መሥመር ዝርጋታው ግድቡ ከተገነባበት ጉባ አንስቶ ብሔራዊ የኤሌክትሪክ ኃይል ቋት እስከሚገኝበት ሆለታ ድረስ ተዘርግቷል ተብሏል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከኃይማኖት አባቶችና ከሲቪክ ማኅበራት ጋር ግድቡን በተመለከተ ዛሬ ውይይት አድርጓል።

የግድቡ ተደራዳሪዎች ቴክኒክ ቡድን አባል ዶክተር በለጠ ብርሃኑ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ የግድቡ ግንባታ በመልካም ደረጃ ላይ ይገኛል።

አሁን ላይ ከግንባታና ከኮንክሪት ሙሌት ጋር ተያይዞ የሚሰራው የግድቡ አጠቃላይ የሲቪል ሥራ 91 ነጥብ 8 በመቶ መድረሱንም ነው የጠቆሙት።

የግድቡ የኤሌክትሮ መካኒካል ሥራው 54 ነጥብ 5 በመቶ እንዲሁም የኃይድሮሊክ ስትራክቸር ደግሞ 55 ነጥብ 2 በመቶ መድረሱን ተናግረዋል።

ይህንንም ተከትሎ አሁን ላይ የግድቡ አጠቃላይ ግንባታ 80 በመቶ መድረሱን ነው የገለጹት።

ከዚህ ጎን ለጎን ከጉባ እስከ ሆለታ የሚደርሰው የ650 ኪሎ ሜትር የግድቡ ኃይል ማስተላለፊያ መሥመር ዝርጋታ ሙሉ በሙሉ ተጠናቋል ነው ያሉት።

ግድቡ ቅድመ ምርት ሲጀምር ወዲያውኑ ኃይል እንዲያስተላልፍ ወደ ሥራ ይገባል ነው ያሉት።

በተጓዳኝም የግድቡ ሁለት ተርባይኖች የቅድመ ኃይል ምርት በመጪው ክረምት መጨረሻ አካባቢ እንደሚጀምርና ለዚህም ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ዶክተር በለጠ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም