እግር ኳስ ለሰላምና አንድነት ያለውን አስተዋጽኦ በመረዳት የቡድኖችን የገንዘብ ችግር መፍታት ይገባል ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
እግር ኳስ ለሰላምና አንድነት ያለውን አስተዋጽኦ በመረዳት የቡድኖችን የገንዘብ ችግር መፍታት ይገባል ተባለ

ግንቦት 11/ 2013(ኢዜአ) የእግር ኳስ ስፖርት ለአገር ሰላምና አንድነት ያለውን አበርክቶ በመረዳት የእግር ኳስ ቡድኖችን የገንዘብ ችግር ለመፍታት መስራት እንደሚገባ ተገለጸ።
ፋሲል ከነማ ስፖርት ክለብ "ስፖርት ለኢትዮጵያ ሕብር" በሚል መሪ ሃሳብ ግንቦት 17 ቀን 2013 ዓ.ም የሚያካሂደውን የገቢ ማሰባሰቢያ መድረክ አስመክልክቶ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።
የክለቡ ፕሬዚዳንትና የጎንደር ከተማ ከንቲባ ሞላ መልካሙ፣ የክለቡ አሰልጣኝ ስዩም ከበደና እውቁ የእግር ኳስ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያን ከ31 ዓመታት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታ እንድታልፍ ያስቻሉት አንጋፋው አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው እግር ኳስ ለአገራዊ አንድነት ሃይል ነው ብለዋል ።
በተለይ እግር ኳስ ወዳድ የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ወንድማማችነትና አንድነትን እንዲያጎለብት እንዲሁም የጎብኚዎች ፍሰት እንዲጨምር ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል።
ለእዚህም ከስምንት ዓመታት በፊት ኢትዮጵያ ከ31 ዓመታት በኋላ በአፍሪካ ዋንጫ የተሳተፈችበትን ክስተት ያነሱት አሰልጣኝ ሰውነት፣ "ክስተቱ በህዝብ መካከል የፈጠረው ብሔራዊ ስሜትና አብሮነት በገሃድ ታይቷል" ብለዋል።
አገራዊ አንድነትና ሰላም የሚፈጥር ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን ለመፍጠር ጠንካራ የእግር ኳስ ክለቦች መፍጠር እንደሚያስፈልግና ፋሲል ከነማንም ከዚህ አኳያ በዘላቂነት ማጠናከር እንደሚገባ አመልክተዋል።
"ፋሲል ከነማን ጨምሮ ሌሎች የእግር ኳስ ቡድኖች ከልመና ወጥተው ራሳቸውን ችለው የሚንቀሳቀሱበት የገቢ ምንጭ እንዲኖራቸው መስራት ይገባል" ነው ያሉት።
በመሆኑም የእግር ኳስ ስፖርት ለአገር ሰላምና አንድነት እንዲሁም ለጤናማ ትውልድ ግንባታ ያለውን አበርክቶ በመረዳት የእግር ኳስ ቡድኖችን የገንዘብ ችግር ለመፍታት መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል።
የጎንደር ከተማ ከንቲባና የክለቡ ፕሬዚዳንት አቶ ሞላ መልካሙ ፋሲል ከነማ ከሁሉም ኢትዮጵያ የተውጣጡ ተጭዋቾችን ያካተተ መሆኑን አመልክተው በተለይም ከ2011 ጀምሮ ለዋንጫ ባሳየው ጥረት፣ በህብረትና መረጋጋት ለስኬት መብቃቱን ገልጸዋል።
በቀደምትነቱ የሚታወቀው የፋሲል ከነማ ክለብ በአገር ውስጥና በውጭ አገራት በርካታ ደጋፊዎች ያሉት የእግር ኳስ ቡድን ቢሆንም በገንዘበ እጥረት ምክንያት በርካታ ፈተናዎች እንዳሉበት አንስተዋል።
"ከተማ አስተዳድር ከጠቅላለ በጀቱ 5 በመቶ ቢመድብም ካለው የዘርፉ ወጭ አንጻር በቂ አይደለም፤ ደጋፊዎቹ የሚመለከቱበት በቂ ስታዲየምም የለውም" ብለዋል።
ቡድኑ በዘላቂነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የራሱ የገቢ ማመንጫ ማዕከላት ለመፍጠርና ተተኪ ተጭዋቾች የሚሰለጥኑበት የወጣቶች አካዳሚ ማቋቋምን ጨምሮ በርካታ እቅዶች ማቀዱን ገልጸዋል።
ከነዚህም መካከል በመጭው ሳምንት ግንቦት 17 በአዲስ አበባ ሸራተን ሆቴል 1 ቢሊዮን ብር ገንዘብ ለመሰብሰብ ያቀደበት የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም (ቴሌቶን) ማዘጋጀቱን አነስተዋል።
ክለቡ በቀጣይ ኢትዮጵያን ወክሎ በአፍሪካ የሚወዳድር ቡድን በመሆኑ ጥንካሬውም፣ ድክመቱም የሁሉም ኢትዮጵያዊያን በመሆኑ ክለቡን በማጠናከር መላው ኢትዮጵያዊያን እንዲሳተፉ ጠይቀዋል።
የቡድኑ አሰልጣኝ ስዩም ከበደ በበኩላቸው ስፖርት በተለይም እግር ኳስ ለሰላም፣ ለፍቅርና ወንድማማችነት መጠናከር አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ በየዘመነ መንግስቱ በርካታ ጠንካራ ክለቦች እየተቋቋሙ በገንዘብ እጥረት ሳቢያ መቀጠል ባለመቻላቸው መክሰማቸውን አንስተዋል።
በዚህ ሁኔታ ለክለቦች መጠንከር ከባድ እንደሆነ ገልጸው፤ የትንሿ ኢትዮዮጵያ ተምሳሌት የሆነውን ፋሲል ከነማንም ጠንካራ ክለብ ሆኖ እንዲዘልቅ ከሞግዚትነት ወጥቶ ራሱን መቻል እንዳለበት ገልጸዋል።
በ1960 ዓ.ም የተመሰረተው ፋሲል ከተማ በ1966 በኢትዮጵያ ሻምፒዮና ሆኖ አጠናቆ ነበር።ዘንድሮም ከ53 ዓመታት በኋላ በኢትዮጵያ ፕሪሜየሪሊንግ አራት ጨዋታዎች እየቀሩት ሻምፒዮን ሆኗል።