ቀጥታ፡

በሽግግር ሂደት በውስን ችግሮች ብቻ ማተኮር ሳይሆን ወደፊት የሚመጣውን መደላደል መመልከት ተገቢ ነው - ምሁራን

 በአዲስ አበባ ግንቦት 11/2013 (ኢዜአ) በሽግግር ሂደት በተወሰኑ ችግሮች ላይ ብቻ ማተኮር ሳይሆን ወደፊት የሚመጣውን መደላደል መመልከትና ለዚያም መተባባር ተገቢ መሆኑን ምሁራን ተናገሩ፡፡


ምሁራኑ ይህንን ያሉት በሠላም ሚኒስቴር አዘጋጅነት እየተካሄደ በሚገኘው አገራዊ የምክክር መድረክ ነው፡፡ 

የምክከር መድረኩ "የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሽግግር ሂደት፣ ብሔራዊ መግባባት፣ ምርጫ 2013 እና ከዚያ ባሻገር" በሚል መሪ ሀሳብ መካሄዱን ቀጥሏል።


"የሽግግር ተሞክሮዎች ንጽጽራዊ ትንታኔ" የሚል የመነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት በስትራቴጂ ጉዳዮች ተቋም ተመራማሪ ዶክተር ሄኖክ ጌታቸው ዴሞክራሲያዊ የሽግግር ሂደት እንዲካሄድ ከውጫዊ ሁኔታ ይልቅ በውስጣዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡


የዴሞክራሲ የሽግግር ሂደትም ሁሉን ባሳተፈ መልኩ ሊካሄድ ይገባል ያሉት ዶክተሩ ሄኖክ፣ ይህ ከሆነ የሕዝቦች የዴሞክራሲ ፍላጎት ይሟላል ብለዋል፡፡


በአንድ አገር የተሳካ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ለማካሄድ የፖለቲካ ፖርቲዎች፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎችና የዴሞክራሲ ተቋማት የራሳቸውን በጎ አስተዋጽኦ ማድረግ እንዳለባቸውም ጠቁመዋል፡፡

  
ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም የተወከሉት ዶክተር ዘላለም ተፈራ በበኩላቸው የሽግግር ሂደት በአንድ ጊዜ ተጀምሮ የሚያልቅ ሳይሆን ጊዜ የሚፈልግ መሆኑን ገልጸዋል።

የሽግግር ሂደትን ለማሳካት ከባቢያዊ ሁኔታን መመልከትና መፍትሄ እየሰጡ መሄድ እንደሚያስፈልግ ነው የጠቆሙት፡፡

  
የፖለቲካ ሽግግር ሲካሄድ እርስ በእርስ መቻቻልና መተባባር ያሥፈልጋል ሲሉም አክለዋል፡፡  

ዶክተር ዘላለም የሽግግር ሂደት በአንድ ጀንበር የሚመጣ ባለመሆኑ ለስኬታማነቱ ሁሉም የራሱን ሃላፊነት ሊወጣ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡


በሽግግር ሂደቱ በውስን ችግሮች ላይ ብቻ ማተኮር ሳይሆን ወደፊት የሚመጣውን መደላደል መመልከት ተገቢ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡

 
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል አንትሮፖሎጂ መምህርና የብዝሃነት ተመራማሪ ዶክተር ካይረዲን ተዘራም የሽግግር ሂደት የመንግስትን ብቻ ሳይሆን የሁሉንም ኅብረተሰብ ተሳትፎ ይጠይቃል ይላሉ።  


ያጋጠሙ ፈተናዎች ጊዜያዊ ናቸው ብሎ ማመንና ችግሮቹንም በትዕግስት ማለፍ እንደሚገባ በመግለጽ፡፡


ሦስተኛ ቀኑን በያዘውና ዛሬ ይጠናቀቃል በተባለው አገራዊ የምክክር መድረክ የሕዝብ ተወካዮች የምክር ቤት አባላት፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የመንግስት ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች፣ የሚዲያ ባለሙያዎችና ምሁራን እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም