አገራዊ መግባባትን ለመፍጠር አንድ በሚያደርጉ ዕሴቶች ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባል --የሰላም ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል - ኢዜአ አማርኛ
አገራዊ መግባባትን ለመፍጠር አንድ በሚያደርጉ ዕሴቶች ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባል --የሰላም ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል
ግንባት 11/2013 (ኢዜአ) አገራዊ መግባባትን ለመፍጠር በልዩነት ላይ ሳይሆን፤ አንድ በሚያደርጉን ዕሴቶች ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ የሰላም ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል ተናገሩ፡፡
"የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሽግግር ሂደት፣ ብሔራዊ መግባባት፣ ምርጫ 2013 እና ከዚያ ባሻገር” በሚል መሪ ሀሳብ የሰላም ሚኒስቴር ያዘጋጀው የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው፡፡
በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የሰላም ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል፤ አገራዊ መግባባትን ለመፍጠር በልዩነት ላይ ሳይሆን፤ አንድ በሚያደርጉን ዕሴቶች ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባል ብለዋል።
ሚኒስቴሩ በኢትዮጵያ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመሥራት ላይ መሆኑንም አብራርተዋል።
ለዚህም ሕዝቡ የተጀመረው አገራዊ መግባባት እንዲሳካ በልዩነቶች ላይ ሳይሆን፤ አንድ በሚያደርጉ ዕሴቶች ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡
ሚኒስቴሩ አገራዊ መግባባት እንዲፈጠር በ14 ሺህ ቀበሌዎች ከ20 ሚሊዮን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን የሚያሳትፉ የምክክር መድረኮች በመካሄድ ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
የብሔራዊ መግባባት አጀንዳውም የጋራ መግባባትን በመፍጠር የመረዳዳት ባህልን ለማዳበር መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም ሕዝብን ማዕከል ያደረገና አሳታፊ የሆነ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ለማምጣት እንደሚረዳ ጠቁመዋል፡፡
በመድረኩ "ጉዞ ወደ ብሔራዊ መግባባት፣ ተግዳሮቶችና መጻኢ ዕድሎች" የሚል የመወያያ ጽሁፍ ያቀረቡት ዶክተር አምባዬ ኦጋቶ፤ ሁሉን ያሳተፈ አገራዊ መግባባትን ማካሄድ ዘላቂ ሠላም ለማምጣት፣ የመቻቻል ባህል ለማዳበርና ልማትን ለማፋጠን ይረዳል ብለዋል፡፡
በአገር ዕድገትና ልማት ዙሪያም የጋራ ራዕይ እንዲኖርና አዲስ ማህበራዊ ቃል ኪዳንና ውል እንዲመሰረትም አገራዊ መግባባት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
"አገራዊ መግባባት የኢትዮጵያን መጻኢ ዕድል ይወስናል" ሲሉም ተናግረዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየትም የሰላም ሚኒስቴር በአገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠር የጀመረው ሂደት ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በመድረኩ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የሚዲያ ባለሙያዎችና ምሁራን ተሳትፈዋል።