ቀጥታ፡

ግብጽና ሱዳን የዓባይን ውሃ በብቸኝነት የመጠቀም ስውር ፍላጎታቸውን ለማሳካት እየጣሩ ነው - አምባሳደር ኢብራሂም እድሪስ

ግንቦት 10 ቀን 2013 (ኢዜአ) ግብጽና ሱዳን ኢትዮጵያን ባገለለ መልኩ የዓባይን ውሃ በብቸኝነት የመጠቀም ስውር ፍላጎታቸውን ለማሳካት እየጣሩ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የድንበርና ድንበር ተሻጋሪ ሀብቶች አማካሪ አምባሳደር ኢብራሂም እድሪስ ገለጹ።

'ስምምነት ሳይደረስ ግድቡ መሞላት የለበትም' የሚለው እ.አ.አ በ2015 ሦስቱ አገራት ከደረሱበት የመርሕ ስምምነት ውጭ በመሆኑ ተቀባይነት እንደሌለው የተደራዳሪ ቡድን አባሉ ኢንጂነር ጌዴዎን አስፋው ተናግረዋል።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ትብብር በሕዳሴው ግድብ ዙሪያ ከፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባላት ጋር ዛሬ ውይይት ተካሂዷል። 

በውይይቱ ላይ የመነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት አምባሳደር ኢብራሂም እድሪስ ግብጽ ከ150 ዓመታት (በፊት) ኢትዮጵያን በኃይል ለመቆጣጠር ስለመሞከሯ የጉራን፣ የጉንደትንና የሐረርን ወረራዋን ለአብነት አንስተዋል።

በከፊልም የጣናን አካባቢ መቆጣጠር ግብ እንደነበራት አውስተው፤ "ግብጽ የምትመራበትን ሕገ መንግስት ጨምሮ በውጭ ፖሊሲዋ የናይል ወንዝ ብቸኛ ታሪካዊ ባለቤት ስለመሆኗ በይፋ አስቀምጣለች" ብለዋል። 

በሌላ በኩል 'ኢትዮጵያ የዝናብ ውሃ አላት፣ በ1929 ውሃውን ተከፋፍለነዋል፣ ውሃ ልትጋሩን አይገባም' በሚል የኢትዮጵያን ልማት የማደናቀፍ ዓላማ እንዳላትም ገልጸዋል።

ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያ በዓባይ ተፋሰስ ልማት እንዳታካሂድ ዓለም አቀፍ ጫና በማድረግ ብድርና እርዳታ እንዳታገኝ መስራቷንም አስታውሰዋል።

"ግብጽና ሱዳን የሕዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ ያለውን አስፈላጊነትና ለእነርሱም ስጋት እንዳልሆነ ያውቃሉ" ያሉት አምባሳደር ኢብራሂም፤ "ውሃውን በብቸኝነት የመጠቀም ስውር ፍላጎታቸውን ማሳካት እየጣሩ ነው" ብለዋል።

ለዚህ ደግሞ በተቻኮለ ስምምነት በማሰር ኢትዮጵያ በዓባይ ተፋሰስ ላይ ለምታከናውናቸው የልማት ፕሮጀክቶች ካይሮና ካርቱም እየሄደች እንድታስፈቅድ ያለመ ፍላጎት እንደሆነ አንስተዋል።

ይህ ደግሞ ከዓለም አቀፍ ሕግ ጋር እንደሚቃረን፣ ከሞራልና ከሃይማኖት አንጻርም ተቀባይነት እንደሌለው ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያን በአስገዳጅ ስምምነት በማሰር የውሃ መብት ማሳጣት ሌላው ዓላማቸው እንደሆነ ገልጸው፤ ይህም የአንዳንድ ምዕራባዊያን ድጋፍ እንዳለበት ተናግረዋል።

ሁለቱ አገሮች ኢትዮጵያን በተቻኮለ ድርድር በማሰር ባለመቻላቸው 'ኢትዮጵያ ግትር ናት' የሚል ትርክት እያራመዱ መሆኑን ገልፀጸዋል።

በአሁኑ ወቅት ሁለቱ አገሮች ከአረቡ ዓለምና ከአውሮፓ ጋር ባላቸው ግንኙነትና የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ በመጠቀም የተለያዩ ዓለም አቀፍ ጫናዎችን ለመፍጠር እየጣሩ መሆኑንም አምባሳደሩ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ውሃው የጋራ ሃብት በመሆኑ የውሃ አጠቃቀሙ ፍትሐዊና ምክንያታዊ መሆን እንደሚገባው እንደምታምንና በዚሁ መርህ እየተንቀሳቀሰች መሆኗንም ገልጸዋል።

"በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ዙሪያ ኢትዮጵያዊያን ያለልዩነት ለስኬቱ በጋራ ሊቆሙ ይገባል" ብለዋል።

የግድቡ ግንባታ የሦስትዮሽ ድርድር ቡድን አባል ኢንጂነር ጌዲዮን አስፋው በበኩላቸው የግድቡ ግንባታ ጥራትና ደህንነት ሁለቱ አገሮች የተስማሙበትና የፈረሙበት መሆኑን ገልጸዋል።

የግድቡ ግንባታ ደህንነት ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን ያሟላና ጥራቱንም አስመልክቶ ያሉ መረጃዎችን ግብጽና ሱዳን በግልጽ እንዲያውቁ መደረጉን አስታውሰዋል።

ግድቡ ከሌሎች ግድቦች በተለየ ውሃው በማስተንፈሻ እየፈሰሰ የሚገነባና ቁመቱ ሲጨምር የውሃ ሙሌቱ እንደሚከናወን ገልጸዋል።

ይህም በመርህ ስምምነቱ በዲዛይኑ ላይ እንዳለና አገራቱም የፈረሙበት በመሆኑ ስምምነት ካላደረጋችሁ አትሞሉም የሚለው ተቀባይነት እንደሌላው አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም