የአገርና የወገን ባለውለታ የሆኑ አረጋዊያንን ማገዝና መደገፍ ይገባል ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
የአገርና የወገን ባለውለታ የሆኑ አረጋዊያንን ማገዝና መደገፍ ይገባል ተባለ

አዲስ አበባ ግንቦት 10/2013/ኤኢዜአ/ የአገርና የወገን ባለውለታ የሆኑ አረጋዊያንን በተገቢው መንገድ ማገዝና መደገፍ እንደሚገባ ተገለጸ።
አረጋዊያንን መደገፍ የችሮታ ጉዳይ ሳይሆን ግዴታና የስራ ሃላፊነት ነው ሲሉ በአዲስ አበባ አስተዳደር በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ጃንጥራር አባይ ገልፀዋል።
"አረጋዊያን ለሕብረ ብሔራዊነት አንድነትና ወንድማማችነት" በሚል መሪ ሃሳብ ለአንድ ወር ሲከበር የቆየው ዓለም አቀፍ የአረጋዊያን ቀን ዛሬ ተጠቃሏል።
በማጠቃለያ መርሃ ግብሩ የተገኙት አቶ ጃንጥራር አባይ በኢትዮጵያ አረጋዊያንን ለመርዳትና ለመደገፍ የተለያዩ ስራዎች ቢከናወኑም በቂ አለመሆናቸውን ገልጸዋል።
አሁን ካለው የአረጋዊያን ቁጥር አኳያ ሁሉንም ለመደገፍ አገሪቷ ያላት አቅም በቂ ቢሆንም በአሰራርና ተያያዥ ችግሮች ምክንያት ተገቢውን ድጋፍና እንክብካቤ ማድረግ አልተቻለም ብለዋል።
የአገር ባለውለታ የሆኑትን አረጋውያን የእውቀትና የታሪክ ሽግግር መሰረት ማድረግ የሚቻለው በቅድሚያ ለእነርሱ መስራት ሲቻል ነው ብለዋል አቶ ጃንጥራር።
አረጋዊያን በበኩላቸው መጪው አገራዊ ምርጫ ሠላማዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን በተለይም ወጣቱ የጥፋት ኃይል ሰለባ እንዳይሆን መምከር እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የአዲስ አበባ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተፈራ ሞላ በበኩላቸው የአረጋዊያንን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያሻሽሉ ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።
ቢሮው በስሩ በሚገኙ ተቋማት በየዓመቱ 7 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር በመመደብ 217 አረጋዊያን የምግብ የመጠለያና የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የአገር ባለውለታ፣ የሠላምና የልማት መገለጫ የሆኑትን አረጋዊያን መንከባከብና መደገፍ ለመንግስት ብቻ የሚተው ተግባር እንዳልሆነም ጠቁመዋል።
በመሆኑም መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ለአረጋዊያን ተብለው የሚከናወኑ ተግባራትን በመደገፍና እነርሱንም በመንከባከብ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡
30ኛው ዓለምአቀፍ የአረጋዊያን ቀን በኢትዮጵያ ለ29ኛ ጊዜ ነው የተከበረው፡፡