የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከግጦሽ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ግጭቶችን ለመፍታት ያግዛል - የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ - ኢዜአ አማርኛ
የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከግጦሽ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ግጭቶችን ለመፍታት ያግዛል - የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ
ግንቦት 10 ቀን 2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ከግጦሽና ውሃ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ግጭቶችን በዘላቂነት ለመፍታት የጎላ ሚና እንዳለው የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አደም ፋራህ ተናገሩ።
ዜጎች መርሃ ግብሩ ያለውን ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ተገንዝበው ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ 7 ቢሊዮን ችግኝ የሚተከልበትን የ2013 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ዛሬ በይፋ ባስጀመሩበት ወቅት የመርሃ ግብሩን አጠቃላይ ሂደት በሚመለከት ውይይት ተካሄዷል።
በመድረኩም የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ አደም ፋራህ እና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎን ጨምሮ የክልል ርእሳነ መስተዳድሮች እንዲሁም ሚኒስትሮች ተሳትፈዋል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አደም ፋራህ፤ መርሃ ግብሩ ከሀገር አቀፍ ባለፈ ቀጠናዊ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይ የአባይ ተፋሰስ ላይ ያለውን የውሃ ፍሰት በመጨመር የታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት በቂ ውሃ እንዲያገኙም እገዛ እንደሚያደርግ ጠቅሰው፤ "ከውሃና ግጦሽ ፍለጋ ጋር በተያያዘ የሚፈጠረውን ግጭት በመቅረፍ ረገድም ፋይዳው የጎላ ነው" ብለዋል።
በመሆኑም ክልሎች በአዋሳኝ አካባቢዎች የሚያከናውኑትን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በጋራ በማቀድ መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በበኩላቸው ባለፉት ሁለት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን አስታውሰው፤ በዘንድሮው መርሃ ግብርም ዜጎች ያለምንም ልዩነት እጅ ለእጅ ተያይዘው ኢትዮጵያን እንዲያለብሱ ጥሪ አቅርበዋል።
"በጋራ በመቆም የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና እውን ማድረግ ይገባል" ብለዋል።
በመድረኩ የተገኙ የክልል ርእሳነ መስተዳድሮችም ችግኝ ከማዘጋጀት ጀምሮ ለመርሃ ግብሩ ማስፈጸሚያ የሚሆን የመሬት ልየታ ማከናወናቸውን ገልጸዋል።
በችግኝ ዝግጅት ረገድም ፍራፍሬን ጨምሮ የተለያዩ የዛፍ ዝርያዎች ችግኝ ማዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
የቀድሞው የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በታሪኳ በደን ሃብት ትታወቅ እንደነበር አስታውሰው፤ ዜጎች በጋራ በመቆም ኢትዮጵያን ማልበስ እንዳለባቸው ጥሪ አቅርበዋል።