ቀጥታ፡

ለሕዳሴ ግድብ ግንባታ ስኬት የበኩላቸውን እንደሚወጡ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ተናገሩ

ግንቦት 10/2013 (ኢዜአ) ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ስኬት ከመንግስት ጎን በመቆም የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ተናገሩ።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ትብብር በህዳሴው ግድብ ላይ ያታኮረ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።

በመድረኩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባላት ተሳትፈዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ዶክተር አረጋዊ በርሄ ግድቡ የሉዓላዊነት፣ የአንድነት፣ የኢኮኖሚ ነጻነት፣ የፍትሃዊ ጥያቄ እና የዜግነት ግዴታ መሆኑን ገልጸዋል።

"ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የእስካሁን ተሳትፎ ጭራ ነበርን" ያሉት ዶክተር አረጋዊ፣ "በአሁኑ ወቅት ህዝብን የወከልን የፖለቲካ ፓርቲዎች የግድቡን ጠቀሜታ በውል አውቀን የመሪነት ሚናችንን መጫወት ይኖርብናል" ብለዋል።

የተለያዩ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በበኩላችው የሕዳሴው ግድብ የሁሉም ኢትዮጵያዊ አሻራ ያረፈበትና የሉዓላዊነት ጉዳይ በመሆኑ ከግብ እንዲደርስ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

ከዚህ በፊት በነበረው ስርዓት የፖለቲካ ፓርቲዎች በሕዳሴ ግድብና መሰለ ፕሮጀክቶች ላይ በጋራ የመምከር እድል እንዳልነበራቸው አንስተው፣ በአሁኑ ወቅት በጋራ መምከር መጀመሩን አድንቀዋል።

በሕዳሴ ግድብ ሳቢያ በኢትዮጵያ ላይ የሚደርሰው የውጭ ተፅዕኖ የአገር ሉዓላዊነት ጉዳይ በመሆኑ ከመንግስት ጎን በመሆን ለአገር ዘብ እንደሚቆሙም አረጋግጠዋል።

በቀጣይም በሕዳሴ ግድብ ላይ በጋራ የሚመከርበትና የሚሰሩበት ሁኔታ በቋሚነት እንዲመቻችም አመራሮቹ ጠይቀዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በበኩላቸው "ሀገር የጋራ ነው፤ የሀገር ጉዳይም በጋራ የምናከናውነው ነው" ብለዋል።

በዕለቱ የተደረገው የምክክር መድረክ ውጤታማ እንደነበር ጠቁመው፤ በቀጣይም በመሰለ መድረኮች ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በቅርበት በመወያይት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም