የኢትዮጵያ ሳምንት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ በይፋ ተከፈተ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሳምንት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ በይፋ ተከፈተ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 10/2013(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ሳምንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ በተገኙበት በወዳጅነት ፓርክ በይፋ ተከፈተ።
የኢትዮጵያ ሳምንት ከዛሬ ጀምሮ እስከ ግንቦት 16 ቀን 2013 ዓ.ም በወዳጅነት ፓርክ ይከበራል።
በዓሉ እንዲከበር ሀሳቡን ያመነጩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሲሆኑ የኢትዮጵያ ሳምንት የሚለውን ዝግጅት እንዲያስተባብሩ ለሦስት ሴት ሚኒስትሮች የቤት ሥራ ተሰጥቷቸው ነበር።
የባህል እና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሒሩት ካሣው፣ የከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን ሚኒስትሯ ኢንጂነር አይሻ መሐመድ እና የሴቶች፣ ወጣቶች እና ሕጻናት ሚኒስትር ፊልሰን አብዱላሂ የባህል ሳምንቱን አስመልክቶ በጋራ ሲዘጋጁ የቆዩ ሲሆን ዝግጅቱን የሚያስተባብር ኮሚቴም ተቋቁሟል።
የዝግጅቱ ዓላማ ሀገሪቱ ያላትን ሀብት እና የተፈጥሮ ፀጋ በማስተዋወቅ ወደ ኢንቨስትመንት መቀየር ነው ተብሏል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ በዛሬው እለት በይፋ በተከፈተው መርሃ ግብር ሁሉም ክልሎች ያሏቸው ልዩ መገለጫዎችና የተፈጥሮ ሃብቶች በተለያዩ ቅርጻቅርፆች፣ በሥዕል እንዲሁም በተንቀሳቃሽ ምሥል በወዳጅነት አደባባይ ለእይታ ቀርበዋል።
በዝግጅቱ ላይ የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች፣ ሚኒስትሮችና ሌሎች የመንግሥት የሥራ ኃለፊዎች ተገኝተዋል።
ኢትዮጵያ በአንድ ቦታ በምትታይበት በእዚህ አውደ ርዕይ ከሁሉም ክልሎች የመጡ የባሕል፣ የታሪክ፣ የተፈጥሮ እና የኢንቨስትመንት ጸጋዎች ለእይታ በቅተዋል።
በዚህ አንድነትን ይበልጥ ለማሳደግ የተዘጋጀው መድረክ ኢትዮጵያ በኢትዮጵያውያን ትወከላለች፤ ሰዎችም እየተዝናኑ ኢትዮጵያን የሚያውቁበት ይሆናል።
የዝግጅቱ ዓላማ በኢትዮጵያ ያሉ ሃብቶችንና የኢንቨስትመንት አማራጮችን ማሳየት፤ አብሮነትን ማሳደግ እንደሆነም ተመላክቷል።
የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ውስጣዊ አንድነትን ማጎልበት እንደሚገባም ተጠቁሟል።
ኢትዮጵያ ከግብርና እስከ ኢንዱስትሪ ያሏትን ሀብቶች ከማስተዋወቅ ባለፈ አገሪቷን ከፍ አድርጎ ለማሳየት ያለመ ሳምንት ነው ተብሏል፡፡
አውደ ርዕዩን ቋሚ ለማድረግ እንደሚሠራና ኢትዮጵያን ወደ አንድ መንደር በማምጣት ቱሪስቶችን የመሳብ ዕቅድም እንዳለው ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ሳምንት አውደ ርዕይ እሴትም ሆኖ እንዲቀጥል የራሱ ሎጎ መዘጋጀቱም ተጠቁሟል።
ለአውደ ርዕዩ የመግቢያ ዋጋ ለተማሪዎች 50 ብር፣ ለአዋቂዎች 200 ብር ሲሆን ህጻናት በነጻ መጎብኘት እንደሚችሉ ተገልጿል።
ከዝግጅቱ የሚገኘው ገቢም ለተፈናቀሉ ዜጎች ማቋቋሚያ ይውላል ነው የተባለው።