ቀጥታ፡

ኢትዮጵያን ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለማሻገር የተከፈለው ዋጋ ውጤት እንዲያመጣ የሁሉንም ጥረት እንደሚጠይቅ ተገለጸ

አዲስ አበባ፤ግንቦት 10/2013(ኢዜአ) ኢትዮጵያን ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለማሻገር እስካሁን የተከፈለው ዋጋ ውጤት እንዲያመጣ ለማስቻል የሁሉም ትብብርና ጥረት ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ።

በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ ታዋቂና ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ኢትዮጵያን ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለማሻገር የተከፈለውን መስዋእትነት ውጤት እንዲኖረው ማድረግ ይገባል ብለዋል።

ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲ መስክ ችግር የሚገጥማት ውስጣዊ የሆነ ችግር ሲጋረጥባት መሆኑን ጠቅሰው፤ ግብጽ ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ፍትሃዊ ተጠቃሚ እንዳትሆን የምትሰራው የህዳሴው ግድብ የቀደመውን ሁሉን አቀፍ ተጠቃሚነት ስለሚነፍጋት መሆኑን አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብ በጋራና በአንድነት የሚቆምበት ሁኔታ በተፈጠረ ቁጥር ኢትዮጵያ በውጭ የሚኖራት የዲፕሎማሲ ተዕእኖ የማደግ አቅም እንዳለው እውቁ ፖለቲከኛና ፀሃፊ አንዳርጋቸው ጽጌ ገልጸዋል።

አሜሪካና የአውሮፓ ሀገራት በአፍሪካ ውስጥ እንደ ልባቸው እንዳይፈነጩ የቻይና ፣ሩሲያና ህንድ ጥንካሬና አጋርነት ፈተና እንደሆነባቸውም አንስተዋል።

"በአገር ውስጥ የራሳቸው ጥቅም ያላቸው ግለሰቦች ጥቅማቸው እስካልተከበረ ድረስ አገር ቢፈርስ ደንታ ስለሌላቸው ከውጭ ኃይሎች ጋር በማበር መስራታቸውን አያቆሙም" ብለዋል፡፡

አሜሪካ ኢትዮጵያን አስመልክታ ያወጣችው መግለጫ ንቀትና ድፍረት የተቀላቀለበት መሆኑንም አንስተዋል።

አሜሪካና የአውሮፓ አገራት ለኢትዮጵያ መሰረታዊ ጥቅም እንደቆሙት እንደ ቻይና፣ ሩሲያና ህንድ በተፎካካሪነት ለመሰረታዊ ጥቅሟ መረጋገጥ መቆም አለባቸው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ሊቀመንበር የሺዋስ አሰፋ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ችግር በተጋረጠባት ወቅት ከጎኗ የቆመ አካል አለመኖሩን ታሪክ ያሳየናል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት፣ የአፍሪካ ህብረትና የኢጋድ መስራችና እንዲሁም በማንኛውም አገር ጉዳይ ጣልቃ ገብታ ባታውቅም በክፉ ቀን ከጎኗ የሚቆም ወዳጅ አልነበራትም ብለዋል፡፡

አሜሪካና መሰሎቿ የሚያስተላልፉት መልዕክት ከራሳቸው ጥቅም አኳያ የተቃኘ መሆኑን በመጠቆም መስማት የሚመርጡት የፈለጉትን ጉዳይ ብቻ ነው ብለዋል፡፡

የዲፕሎማሲና የውጭ ግንኙነት ምስረታው አገረ መንግስቱን ያላከበረ ከሆነ መደፋፈር ስለሚሆን በወጣው መግለጫ ልክ ምላሽ መስጠት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በአገራዊ ጥቅም ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ልዩነትም ሆነ ውድድር ሊኖር እንደማይገባና በዚህ ጉዳይ ላይ "የፖለቲካም ሆነ የሃይማኖት ልዩነት ሳይገድበን በጋራ መቆም አለብን" ብለዋል፡፡

"ኢትዮጵያን ወደ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለማሻገር መስዋዕትነት ከተከፈለ በኋላ ወደ ኋላ ለመመለስ የሚደረገው ጥረት ተቀባይነት የሌለው ነው" ሲሉም አንስተዋል።

ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ግዙፍ አገር መሆኗን ተከትሎ ጉዞዋን ወደ ኋላ ለመጎተት የተለያዩ ሴራዎች እየተከናወኑ እንደሆነና ከኢትዮጵያ ጋር ተጣልቶ በቀጠናው ሰላምን ማረጋገጥ የማይታሰብ መሆኑን አክለዋል፡፡

ምዕራባውያኑ ምርጫው ለአገሪቱ መጻኢ ዕድል ወሳኝ በመሆኑ እንዳይከናወን፤ ከተካሄደም በኋላ የምርጫውን ሂደት በማጥላላት ተጨማጭ ያልሆነ ምክንያት በመስጠት ቅቡልነቱን እንዲያጣ እጃቸውን በማስገባት አገሪቱን ማተራመስ አንደሚፈልጉ የፍልስፍና ምሁሩ ዮናስ ዘውዴ /እጩ ዶክተር/ ተናግረዋል፡፡

ያንን የሚያሳዩ በርካታ ምልክቶች መኖራቸውንም ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ኃይል ካገኘችና ጠንክራ ከወጣች ምን አይነት አገር እንደምትሆን ቀድሞ ስለገባቸው አገሪቱን ለማተራመስ ቆርጠው መነሳታቸውንም ተናግረዋል፡፡

ምዕራባውያኑ የኢትዮጵያ አገረ መንግስት እንዳይቀጥል ፍላጎት ስላላቸው እንጂ ከእኛ በላይ ስለእኛ አስበው አይጨነቁም ነው ያሉት።

"እንደ አገር የውስጥ ችግሮቻችንን ይዘን መዝለቃችን እኛነታችንን ፣ህልውናችንንና የአገራችንን ገጽታ ሊያሳጣን በሚችል ደረጃ ላይ እንድንቀመጥ ስላደረገን የጋራ አቋም መያዝ አለብን" ያሉት ደግሞ የእስልምና ሃይማኖት መምህሩ ኡስታዝ አበቡበከር አህመድ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም