የኢትዮጵያ ቅርሶች ለትውልድ እንዲተላለፉ ለማድረግ ሙዚየሞችን በመገንባት ታሪክን መሰነድ እንደሚገባ ተጠቆ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ቅርሶች ለትውልድ እንዲተላለፉ ለማድረግ ሙዚየሞችን በመገንባት ታሪክን መሰነድ እንደሚገባ ተጠቆ
አዲስ አበባ ግንቦት 10/2013/ኤኢዜአ/ የኢትዮጵያ ቅርሶች ለትውልድ እንዲተላለፉና የቱሪስት መስህብ እንዲሆኑ ለማድረግ ሙዚየሞችን በመገንባት ታሪክን መሰነድ እንደሚገባ ተጠቆመ።
የኢትዮጵያ ባህል ቱሪዝም ጋዜጠኞች ማህበር ከአዲስ አበባ ሙዚየም ጋር በመተባበር "የሙዚየም መፃኢ ጊዜ ታድሶና አዲስ ዕይታ" በሚል መሪ ሃሳብ የአለም የሙዚየም ቀን ለመጀመሪያ ጊዜ አክብረውታል፡፡
የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ ወይዘሪት ፋይዛ መሃመድ እንዳሉት ኢትዮጵያ በአገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ የበርካታ ቅርሶች ባለቤት ናት፡፡
ቅርሶችን በተደራጀ መልኩ በማስቀመጥ ለቱሪስት መስህብ ለማድረግና ለትውልድ ለማስተላለፍ በቀጣይም ተጨማሪ ሙዚየሞችን በጋራ መገንባት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
ከአገር የወጡ ቅርሶችን ለማስመለስ ቅድሚያ የተደራጀ ሙዚየም ስለሚያስፈልግ ነባሮቹን ሙዚየሞች የማስተካከል ስራ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ያለፈውንና የአሁኑን ታሪክ አጣምራ የያዘች የህይወት ሚስጥር በመሆኗ ባህልና እሴቶቿን ለመጠበቅ ሙዚሞችንና የባህል ማዕከላትን ምቹ ማድረግ ይገባል ብለዋል ኃላፊዋ፡፡
ለዚህ ስኬት የጋራ ትብብርን ይጠይቃል ሲሉም አስገንዝበዋል።
በአፍሪካ በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ ሃብት ከሚጠቀሱ አገሮች መካከል አንዷ ኢትዮጵያ ናት ያሉት ወይዘሪት ፋይዛ ይህንን ሃብት የገቢ ምንጭ ለማድረግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ባህል ቱሪዝም ጋዜጠኞች ማህበር ፕሬዘዳንት ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም፤ ማህበሩ አገሪቱ ያላትን የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ቅርሶችና ሃብቶች የቱሪስት መስህብ ለማድረግ የማስተዋወቅ ስራ እየሰራ መሆኑን ተናግሯል ፡፡
አንዳንድ አገራት የተፈጥሮና የሰው ሰራሽ ቅርስ ሳይኖራቸው በየቀኑ ሙዚየሞቻቸው በብዙ ሰዎች እንደሚጎበኙ በመጥቀስ በአገራችን ሙዚየም የመጎብኘት ባህላችን ዝቅተኛ ነው ሲሉም አንስቷል።
የአገር ውስጥ ጎብኝዎች የመጎብኘት ባህል እንዲዳብር ማህበሩ ከባለድርሻዎች ጋር በትብብር እንደሚሰራም ገልጿል፡፡
ከኢትዮጵያ ተዘረፈው በአውሮፓ አገራት የሚገኙ የብራና መጽሃፍት ፣ አልባሳቶች ፣ መስቀሎችና ፅናጽሎች በተደራጀ መልኩ በማጥናት ወደ አገር ማስመለስ አንደሚገባ ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ ተናግሯል፡፡
ለዚህም የተጠናከረ የዲፕሎማሲ ስራዎች መስራት እንደሚያስፈልግ ነው የገለጸው፡፡
ቅርሶችን ወደ አገር ውስጥ በማስመለስ፣ በተደራጀ ሙዚየም በማስቀመጥና በመሰነድ ለጥናትና ምርምር ማዋል ይገባልም ብሏል፡፡