አገራዊ መግባባት የኢትዮጵያን መጻኢ ዕድል ይወስናል - ዶክተር አምባዬ ኦጋቶ - ኢዜአ አማርኛ
አገራዊ መግባባት የኢትዮጵያን መጻኢ ዕድል ይወስናል - ዶክተር አምባዬ ኦጋቶ
አዲስ አበባ ግንቦት 10/2013/ኤኢዜአ/ አገራዊ መግባባት ወይም ምክክር የኢትዮጵያን መጻኢ ዕድል ይወስናል ሲሉ በጀስቲስ ፎር ኦል ከፍተኛ የሠላምና የምክክር ሂደት አማካሪ ዶክተር አምባዬ ኦጋቶ ገለጹ።
ዶክተር አምባዬ ይህን የገለጹት "የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሽግግር ሂደት፣ ብሔራዊ መግባባት፣ ምርጫ 2013 እና ከዚያ ባሻገር" በሚል በሠላም ሚኒስቴር አዘጋጅነት እየተካሄደ ባለው የምክክር መድረክ ነው።
በምክክር መድረኩ "ጉዞ ወደ ብሔራዊ መግባባት፣ ተግዳሮቶችና መጻኢ ዕድሎች" በሚል የመወያያ ጽሁፍም አቅርበው ውይይት እየተካሄደ ይገኛል።
ዶክተሩ በጽሁፋቸው አዲሱ የለውጥ መንግስት በኢትዮጵያ አዲስ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ አቅጣጫዎችን ይዞ መምጣቱን ገልፀዋል።
በዚህም በርካታ ሕዝብ ተጠቃሚ ያደረጉ ስራዎች መከናወናቸውን አብራርተዋል።
በሌላ በኩል በሶስት ዓመቱ የለውጥ ጉዞ የኑሮ ውድነት፣ ስራ አጥነት፣ በተለያዩ ቦታዎች የተፈጠሩ የሠላም እጦቶችና የዜጎች መፈናቀል ተግዳሮቶችን ጠቅሰዋል።
በመሆኑም በኢትዮጵያ አገራዊ መግባባት መፍጠር ዘላቂ ሠላም እንዲመጣ፣ የመቻቻል ባህል እንዲዳብርና አፋጣኝ ልማት እንዲኖር ያስችላል ብለዋል።
በአገር ዕድገትና ልማት ዙሪያ የጋራ ራዕይ እንዲኖርና አዲስ ማኅበራዊ ቃል ኪዳንና ውል እንዲመሰረትም አገራዊ መግባባት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
እንደ ዶክተር አምባዬ ገለጻ አገራዊ መግባባት መፍጠር የኢትዮጵያን መጻኢ ዕድል ይወስናል።
በአገራዊ የምክክር መድረኩ የሠላም ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ የሚዲያ ባለሙያዎችና ምሁራን እየተሳተፉ ነው።