ጀነራል ዊንጌት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የተመሰረተበትን 75ኛ ዓመት አከበረ - ኢዜአ አማርኛ
ጀነራል ዊንጌት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የተመሰረተበትን 75ኛ ዓመት አከበረ

ግንቦት 10 / 2013 (ኢዜአ) የጀነራል ዊንጌት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የተመሰረተበትን 75ኛ ዓመት የአልማዝ ኢዮቤልዩ በዓል አክብሯል።
የቀድሞው የጀነራል ዊንጌት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የአሁኑ የጀነራል ዊንጌት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ 75ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ዛሬ በትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ አክብሯል።
በዝግጅቱም ቀደም ሲል በኮሌጁ የተማሩና በኢትዮጵያ በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ አሻራቸውን ያሳረፉ ግለሰቦች ታድመዋል።
በመድረኩ ኮሌጁ ባለፉት 75 ዓመታት ያከናወነውን ታሪካዊ ሂደት የሚያሳይ ገለጻ ተደርጓል።
ኮሌጁ በ1938 ዓ.ም በሁለት አሮጌ ክፍሎች በትምህርታቸው ከፍተኛ ውጤት ያመጡ 30 ተማሪዎችን በመቀበል ማስተማር እንደጀመረ ተገልጿል።
ለ31 ዓመታት የቀለም ትምህርት በመስጠት ሲያገለግል ቆይቶ ከ1973 ዓ.ም ጀምሮ የኮንስትራክሽን ሙያ በመስጠት በርካቶችን የሙያ ባለቤት እንዳደረገም ተመላክቷል።
በትምህርት ሚኒስቴር በ1994 ዓ.ም ተሻሽሎ የወጣውን የቴክኒክና ሙያ ትምህርት እና ሥልጠና ስትራቴጂ በመከተል ተማሪዎችን በ10ኛ ክፍል ውጤት በመቀበል በተለያዩ ሙያዎች ሲያሰለጥን መቆየቱም ተገልጿል።
ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ ወደ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ደረጃ በማደግ በአሁኑ ወቅት 625 ተማሪዎችን በመጀመሪያ ዲግሪ እያስተማረ እንደሚገኝም ተገልጿል።
የኮሌጁ ዲን አቶ መለሰ ይመር በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ኮሌጁ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በማሻሻል እንዲሁም አዳዲስ የፈጠራ ውጤቶች ተባዝተው ለህብረተሰቡ እንዲደርስ እያደረገ ነው።
የዓለም ባንክ ያወጣውን ውድድር በማሸነፍ በምስራቅ አፍሪካ የልህቀት ማዕከል ለመሆን ተመርጦ የ14 ነጥብ 85 ሚሊየን ዶላር ፈንድ ተጠቃሚ መሆኑንም ገልጸዋል።
የ75ኛ ዓመት ኢዮቤልዩ በዓል የመከበሩ ዓላማም በአሁኑ ወቅት በተለያየ የኃላፊነት ቦታ የሚሰሩ የቀድሞ የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች አሁን ላሉት የ’ይቻላል’ መንፈስን ለመፍጠር እንደሆነም አስረድተዋል።
የምስረታ በዓሉ ለአንድ ወር በተለያዩ ሁነቶች እንደሚከበርም አስታውቀዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቴክኒክና ሙያ ትምህርት እና ሥልጠና ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ተክሉ ሽኩር ኮሌጁ በቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ ትልቅ አሻራን እያሳረፈ እንደሆነ ተናግረዋል።
በቀጣይም የፈጠራ ውጤቶችን በማዳበር ለላቀ ስኬት መሥራት እንደሚገባ ጠቁመው፤ ኤጀንሲው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።
የጀነራል ዊንጌት ትምህርት ቤት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፣ ደራሲ በዓሉ ግርማ፣ የዓለም ሎሬት ሜተር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ፣ ፕሮፌሰር አክሊሉ ለማን እና ሌሎችንም ታላላቅ ሰዎች ያፈራ አንጋፋ ትምህርት ቤት ነው።
የትምህርት ቤቱ ስያሜ፤ ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት አርበኞችን ለማገዝ በምዕራብ ኢትዮጵያ የእንግሊዝን ጦር ሲመራ በነበረው ጀነራል ኦርድ ቻርለስ ዊንጌት ማስታወሻነት እንደሆነም መረጃዎች ያሳያሉ።