ቀጥታ፡

ለምርጫው ስኬታማነት ተቀናጅተው እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ

ሆሳዕና ግንቦት 10/2013 (ኢዜአ) ለስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬታማነት ተቀናጅተው በቁርጠኝነት እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን በከንባታ ጠምባሮ ዞን የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ።

ፓርቲዎቹ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በምርጫው የህዝቡን ተሳትፎ በማጎልበት ሰላማዊነቱ፣ ተዓማኒነቱና ዲሞክራሲያዊነቱ በተግባር እንዲረጋገጥ አበክረው እየሰሩ ነው።

የብልጽግና ፓርቲ  ጽህፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ  የከንባታ ጠምባሮ ዞን ኃላፊ አቶ ሰላሙ ማዴቦ በሰጡት አስተያየት፤ምርጫውዜጎች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነታቸው ሊያረጋግጡላቸው የሚችሉ ተወካዮቻቸውን የሚመርጡበት ብቸኛው መንገድ በመሆኑ ለዚህ መሳካት  ፓርቲው በቁርጠኝነት  እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ምርጫው በሀገሪቱ የተጀመሩ የለውጥ ስራዎች ቀጣይነት እንዲኖራቸው ወሳኝ በመሆኑ ሰላማዊነቱን፣ ተዓማኒነቱንና ዲሞክራሲያዊነቱ እንዲረጋገጥ አቋም ተይዞ ርብርብ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ብልጽግና ፓርቲን ወክለው በምርጫው የሚወዳደሩ ዕጩዎች ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ካለምንም የፀጥታ ችግር የምረጡኝ ቅስቀሳ በይፋ እያካሄዱ መሆኑን ጠቁመዋል።

የዞኑ ህዝብም  በምርጫውበንቃትበመሳተፍ ይበጀኛል የሚለውን አካል እንዲመርጥ ከወዲሁ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን አስታውቀዋል።

በዞኑ የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ባቋቋሙት የጋራ ምክር ቤት አማካኝነት እየተገናኙበመምከር ለምርጫው ስኬታማነት ቅንጅት ፈጥረው  እየተንቀሳቀሱ እንደሚኙ ተናግረዋል።

በምርጫው አሸናፊው ሆኖ ለወጣው አካል  ሙሉ ድጋፍ በመስጠት ሀገሪቱን በሠላም ለማሸጋገር ከምንጊዜውም በላይ ፍላጎታቸውን በተጨባጭ እያሳዩ እንደሆነም ኃላፊው አብራርተዋል።

የህብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የከንባታ ጠምባሮ ዞን ሊቀመንበር አቶ አድማሱ ጎታ  በበኩላቸው፤  የዞኑ ህዝብ ለአካባቢው ሠላም ዘብ በመቆም በምርጫው የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግ  ፓርቲያቸው በየደረጃው ግንዛቤ የመፍጠር ስራ እያከናወነ መሆኑን  ገልጸዋል።

ፓርቲው በሂደት  የሚያጋጥሙትን ተግዳሮቶች በጋራ ምክር ቤቱ እየፈታ በምርጫው ለማሸነፍ የሚያበቃውን ጠንካራ እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ማናቸውንም ችግሮች በመቋቋም ጠቅላላው ምርጫ ሰላማዊ፣ፍትሐዊ፣ ነፃና በህዝብ ዘንድ ቅቡልነትን ያተረፈ እንዲሆን አበክረው እየሰሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ የዞኑ ሊቀመንበር አቶ አለማየሁ ገበረጽዮን ፓርቲያቸው እንደ ሀገር ሰፊ የሆነ የፖለቲካ ምህዳር ባልተፈጠረበት ወቅት ጭምር በሰላማዊ መንገድ ሲታገል የቆየ ዲሞክራቲክ መሆኑን አውስተዋል።

አሁን ላይ የተፈጠረውን  ሰፊ የፖለቲካ  ምህዳር በመጠቀም  ሰላማዊና  ፍትሃዊ  ምርጫ እንዲካሄድና  ህብረተሰቡም  የነቃ ተሳትፎ እንዲያደረግ ስትራቴጂ ነድፈው ለተግባራዊነቱ እየሰሩ መሆናቸውን አመልክተዋል።

በስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ለህዝብ ተወካዮችና ክልል ምክር ቤቶች ብልጽግና ፓርቲ  24 ዕጩዎች፣ የህብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ  አራት እና የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ  ደግሞ 34 ዕጩዎች በከንባታ ጠምባሮ ዞን ለመወዳደር ማቅረባቸውን የፖርቲዎቹ አመራሮች  አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም