ቀጥታ፡

ኢዜማ ዜጎች ያለ ስጋት ሰርተው የመኖር መብታቸው እንዲረጋገጥ እንደሚሰራ ገለጸ

ደሴ፤ ግንቦት 10/2013(ኢዜአ) ዜጎች በየትኛውም አካባቢ ያለ ስጋት በመስራት ሀብት አፍርቶ የመኖር መብቱ በተግባር እንዲረጋገጥ አበክሮ እንደሚሰራ የኢትዮጵያ ዜጎች ማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ /ኢዜማ/ አስታወቀ።

ፓርቲው ማንፌስቶውንና ፕሮግራም በደሴ ከተማ  ለአባላትና ደጋፊዎቹ አስተዋውቋል።

በትውውቁ ስነ-ስርዓት የፓርቲው መሪ  ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ "ከዚህ በፊት በተዘራው የዘር ጥላቻና ልዩነት ዜጎች በማንነታቸው ብቻ ከአካባቢያችን ውጡልን በሚል ተወልደው ባደጉበት ቀዬ ባይተዋር ሲሆኑ እንደመመልከት የሚያሳዝን ነገር የለም" ብለዋል፡፡

ይህንን ችግር በማቃለል በኢትዮጵያ አስተማማኝ ሰላምና አንድነት ለመገንባት ፓርቲው በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

ለዚህም ማንኛውም ዜጋ በየትኛውም ክልልና አካባቢ ያለ ስጋት ሰርቶና ሀብት አፍርቶ በነጻነት መኖር የሚያስችል ፖሊሲ ቀርፀው እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

"ቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን ፓርቲው የድርሻውን ይወጣል፤ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ከምን በላይ የሀገርንና ህዝብን ደህንነትን ማስቀደም ይጠበቅባቸዋል" ብለዋል፡፡

ኢዜማ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በማስጠበቅ ቅድሚያ ለአንድነትና ሰላም ከሚሰራ ማንኛውም ፓርቲ፣ ቡድንና ግለሰብ ጋር በቅንጅት ለመስራት ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።

በአንጻሩ ለመመረጥና ለፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ስንል ከታሪካዊ የውጭና የውስጥ ጠላቶቻችን ጋር አንደራደርምም ያሉት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፤በሀገሪቱ የተንሰራፋውን የህዝብን ሀብት መመዝበር እንደማይታገሱ ገልጸዋል።

በቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫም በመላው የሀገሪቱ ክፍል እንደሚወዳደሩ ጠቁመው ህብረተሰቡ ተረጋግቶ ለሚፈልገው ፓርቲ ድምጹን በመስጠት የዜግነት ግዴታውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በትውውቁ መድረክ ከተሳተፉት መካከል አቶ መሃመድ አህመድ እንዳሉት፤  እየተባባሰ የመጣውን የሰላም እጦትና የመለያየት አባዜ ለማስቆም ፓርቲዎች ተቀራርበው መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡

ሀገርና ህዝብ ሲኖር ብቻ ነው መመረጥም ሆነ መምረጥ የሚቻለው ያሉት አቶ መሃመድ፤ ዜጎች በሀገራቸው ላይ በግፍ እንዳይገደሉና እንዳይፈናቀሉ ለማድረግ ሁሉም ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

ሀገሪቱ ከገጠማት ውስብስብ ችግር እንድትላቀቅና ሉዓላነቷ እንዲጠበቅ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ከመንግስት ጋር ተቀራርበው መስራት እንደሚኖርባቸው የገለጹት ደግሞ ሌላው ተሳታፊ አቶ ታደሰ አለሙ ናቸው፡፡

ለምርጫ ቅስቀሳ ብቻ ለህዝቡ የማይሆን ቃል እየገቡ ትዝብት ላይ ከሚወደቅ የሚሰሩትን ብቻ በማስተዋወቅ ለህዝቡ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ይጠበቅባቸዋልም ብለዋል፡፡

በዚህ አስቸጋሪ ወቅት የኢትዮጵያን አንድነትና ሰላም በተግባር አረጋግጦ ሀገሪቱን ለመቀራመት ካሰፈሰፉ የውጭና የውስጥ ጠላቶች የሚጠብቅ መንግስት የሚያስፈልግ በመሆኑ ካርዳቸውን በአግባቡ እንደሚጠቀሙበት ገልጸዋል።

በተለይ ህብረተሰቡን በዘርና በእምነት እየከፋፈሉ በህዝብ ደም ለሚነግዱ የሴራ ፖለቲከኞች ቦታ የለንም ያሉት አቶ ታደሰ ሉዓላዊነቷ የተጠበቀች ሀገር ለትውልድ ለማስተላለፍ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡

ተመሳሳይ የትውውቅ መረሃ ግብር በሰቆጣ፣ ወልድያና ሌሎችም ከተሞች እንደሚቀጠልም በመድረኩ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም