ባለስልጣኑ ከ45 ሚሊዮን ብር በላይ ያደራጀው የምግብ ጥራት ምርመራ ላቦራቶሪ ለአገልግሎት በቃ - ኢዜአ አማርኛ
ባለስልጣኑ ከ45 ሚሊዮን ብር በላይ ያደራጀው የምግብ ጥራት ምርመራ ላቦራቶሪ ለአገልግሎት በቃ
አዲስ አበባ ግንቦት 10/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ የምግብና መድሃኒት ባለስልጣን ከ45 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በአዲስ መልክ ያደራጀው የምግብ ጥራት ምርመራ ላቦራቶሪ ለአገልግሎት በቃ።
የኢትዮጵያ የምግብና መድሃኒት ባለስልጣን በአዋጅ ቁጥር1112/2011 በተሰጠው ተግባርና ሃላፊነት ቁጥጥር ከሚያደርግባቸው ምርቶች መካከል ምግብ አንዱ ነው።
ባለስልጣኑ ሃላፊነቱን ለመወጣት ዘመኑ ባፈራቸው መሳሪያዎች ያደራጀውን የምግብ ምርመራ ጥራት ላቦራቶሪ ዛሬ አስመርቋል።
ቤተ ሙከራው የተደራጀበትን ህንጻ ለማሳደስ 5 ሚሊዮን ብር፤ ዘመናዊ የላቦራቶሪ መሳሪያዎችን ለማሟላትም ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉ ተገልጿል።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሪት ሂራን ገርባ ምግብ ከባዕድ ነገር ጋር ተቀላቅሏል የሚል ጥቆማ በየጊዜው ለባለስልጣኑ እንደሚደርሰው ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ በጥቆማው መሰረት እርምጃ ለመውሰድ በሚደረግ ሂደት የቤተሙከራ መሳሪያ አለመሟላት ተቋሙ ፈጣን ምላሽ እንዳይሰጥ እንቅፋት ሆኖ መቆየቱን ገልጸዋል።
በአዲስ መልክ የተደራጀው ላቦራቶሪ ችግሩን እንደሚቀርፍና በአንድ ጊዜ ከ200 በላይ ተመሳሳይ ምርቶችን በመመርመረ የጥራት ደረጃቸውን ማረጋገጥ እንደሚችል አስረድተዋል።
"ቀደም ሲል የነበረው ላቦራቶሪ ውስንነት ነበረበት" ያሉት ዳይሬክተሯ ለዚህም ከእድሳቱ በፊት በዘጠኝ ወራት 655 ከውጭ የገቡ ምርቶችን ብቻ መመርመሩን ጠቅሰዋል።
የቤተ ሙከራው በአዲስ መልክ መደራጀት ይህን የውስንነትም ያስቀራል ነው ያሉት።
የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰም ለኅብረተሰቡ ጥራትና ደህንነቱ የተረጋገጠ ምርት እንዲቀርብ የአሰራር ዘዴን ማዘመን እንደሚገባ ተናግረዋል።
የሚታመን ውጤት ለመስጠት ዘመኑ ያፈራቸውን የቤተ ሙከራ መሳሪያዎች ማሟላት ግዴታም እንደሆነ ነው ያመለከቱት።
በኢትዮጵያ ምግብን ከባዕድ ነገር ጋር መቀላቀል፣ሕገወጥ የምግብ ዝውውርና የምግብ በተለያዩ ነገሮች መበከል የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች መሆናቸውንም ዶክተር ሊያ ጠቁመዋል።
በምግብ ላይ ተገቢውን ቁጥጥር በማድረግ የኅብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ ዘመናዊ ላቦራቶሪ መገንባት ወሳኝ መሆኑንም በአጽንኦት ገልጸዋል።
የምግብ ደህንነት ቀን ሰኔ 7 ቀን 2013 ዓ.ም በኢትዮጵያ የምግብና መድሃኒት ባለስልጣን አስተባባሪነት "አሁን ዛሬ ደህንነቱ የተጠበቀ ምግብ ለነገ ጤንነት በሚል መሪ ሃሳብ እንደሚከበር ተገልጿል።