ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ጉዳይ ጣልቃ የሚገቡ የውጭ አገራትን የሚያወግዝ ንቅናቄ ሊካሄድ ነው

ግንቦት 10 / 2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ጉዳይ ጣልቃ የሚገቡ የውጭ አገራትን የሚያወግዝ ንቅናቄ በመላው አገሪቱና በዓለም አቀፍ ደረጃ ሊካሄድ ነው።

የንቅናቄው መርሃ ግብር 'ብሔራዊ ክብር በሕብር' በሚል መሪ ሃሳብ የሚካሄድ ሲሆን ከኢትዮጵያ ሲቪክ ማህበራት፣ አርቲስቶች፣ ከማህበረሰብ አንቂዎችና ከአገር ወዳድ ግለሰቦች የተውጣጡ አካላት ዛሬ ጉዳዩን አስመልክተው ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሞችና የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ሉአላዊነትን የሚዳፈሩ መግለጫዎችን አንዳንድ የውጭ ሀገራት እያወጡ መሆኑን ገልጸዋል።

በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴው ግድብ የውሃ ሙሌት፣ የህግ የማስከበር ዘመቻና የዜጎች መብት የሆነውን የምርጫ ስርዓት አስታከው ጫና ለመፍጠር እየሰሩ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በቅርቡም የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በኢትዮጵያ ላይ ያወጣው መግለጫ የራሷን ችግር በራሷ የመፍታት መብቷን የሚጋፋና ሉአላዊነቷን የጣሰ እንደሆነ አብራርተዋል።

ጉዳዩ መንግሥት ብቻ ላይ ያነጣጠረ ሳይሆን በዋናነት በነፃነትና በጀግንነት በኖረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ እንደሆነ በመግለጫው ተመልክቷል።

ድርጊቱ ኢትዮጵያዊያንን የመናቅ፣ ታሪካቸውን የመዘንጋትና ያልተገባ አመለካከት መኖሩን ያሳዩበት አጋጣሚ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ፖለቲከኛና ጸሐፊ አንዳርጋቸው ጽጌ እንዳሉት፤ ምዕራባዊያኑ በኢትዮጵያ ጉዳይ ጣልቃ እየገቡ የሚያሳድሩትን ተጽእኖ እና የሉአላዊነት ጉዳይ ሕዝቡ ሊቃወም ይገባል።

"ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ቆመው ክብራቸውንና አንድነታቸውን የሚጋፉ አካላትን በማውገዝ በአገራቸው ጉዳይ የማይደራደሩ መሆናቸውን በተግባር ማሳየት ይጠበቅባቸዋል" ብለዋል።

የእስልምና ሃይማኖት መምህሩ ኡስታዝ አቡበከር አህመድ በበኩላቸው ምዕራባውያኑ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ችግሮች በማየት ሉአላዊነቷን የሚዳፈር ተግባር እየፈጸሙ መሆኑን ገልጸዋል።

"በዚህ ወቅት ኢትዮጵያዊያን የፖለቲካና ለሌሎች ልዩነቶችን በመተው ለሀገራቸው ህልውና እና ሉአላዊነት በጋራ መቆም አለባቸው" ብለዋል።

"ኢትዮጵያዊያን በአገራዊ ጥቅማችንና በክብራችን የማንደራደር መሆናችንን በተግባር ማሳየት አለብን" ነው ያሉት።

አርቲስት ዘለቀ ገሰሰ በበኩሉ "የቀደሙ አባቶች ከውጭ የሚመጣባቸውን ወራሪ ሃይል በጋራ እንደመከቱት ሁሉ የአሁኑ ትውልድም በብሔራዊ ጥቅሞቻችን ላይ እየተባራከተ የመጣውን የውጭ ጣልቃ ገብነት ለመመከት በጋራ መቆም አለበት" ብሏል።

በንቅናቄውም ከዛሬ ጀምሮ በመላው አለም በሚገኙ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ዲጂታል የፊርማ ማሰባሰብ ፕሮግራም ይካሄዳል ተብሏል።

የፊታችን አርብ ማለዳ ከተለያዩ ታዋቂ ግለሰቦችና አርቲስቶች የተውጣጡ ግለሰቦች በአገሪቱ ባሉ ኤምባሲዎች የተዘጋጁ ደብዳቤዎች ይሰጣሉ።

ሁሉም ኢትዮጵያዊና ትውልደ ኢትዮጵያውያን አርብ ከቀኑ 10 ሰዓት እስከ 11 ሰዓት የኮቪድ-19 ፕሮቶኮልን በጠበቀ መንገድ በአካበቢው ''እጃችሁን ከኢትዮጵያ ላይ አንሱ'' የሚል መልዕክት ያስተላልፋሉ።

የተጀመረው ንቅናቄ ግቡን እንዲመታ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የበኩሉን እንዲወጣም አስተባባሪዎቹ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም