ቀጥታ፡

ለዘላቂ ሠላም ግንባታ በሚደረገው ጥረት ሕዝቡ የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ ግንቦት 10/2013/ኢዜአ/ ለዘላቂ ሠላም ግንባታና አገራዊ መግባባት ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት ኅብረተሰቡና የሚመለከታቸው አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ ሁሉን አቀፍ አገራዊ ምክክር ኢኒሼቲቭ /ማይንድ ኢትዮጵያ/ ጥሪ አቀረበ።

ኢኒሼቲቩ በኢትዮጵያ አገራዊ መግባባት ለመፍጠር በማለም ሁሉን አቀፍ አገራዊ ምክክር ለማካሄድ በዝግጅት ላይ መሆኑን ገልጿል።

የማይንድ ኢትዮጵያ አባል አቶ ንጉሱ አክሊሉ ኢኒሼቲቩ ሁሉን አቀፍ አገራዊ የምክክር መድረክ አስፈላጊነትን በማመን ለዚሁ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የምክከር መድረኩ በጥበብና ሙያ እንዲሁም በሥነምግባር መመራት ያለበት በመሆኑ ለስኬታማነቱ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

መላ የአገሪቱ ዜጎች በአደረጃጀቶቻቸው አማካኝነት ለውይይት የሚሆኑ አጀንዳዎችን እንዲያቀርቡ እየተደረገ መሆኑንና የምክክር መድረኩን የሚመሩ ሰዎችን በጥቆማ እየቀረቡ እንደሆነም ተናግረዋል።

በምክክር መድረኩ የሚሳተፉ ዜጎች በፆታ፣ በዕድሜ፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ አመለካከት፣ በክልል፣ በትምህርት ዝግጅት ስብጥር እንዲኖራቸው መመሪያ መዘጋጀቱንና ከአንድ ሺህ በላይ ዜጎች እንዲሳተፉ መታቀዱንም አቶ ንጉሱ ጠቁመዋል።

የታሰበው አገራዊ ምክክር የሁሉንም ዜጋ ቀና ትብብር የሚጠይቅ በመሆኑ ዘላቂ ሠላምና የጋራ መግባባት ለማምጣት በሚደረግ ጥረት የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ጎረቤት አገራትና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ከኢኒሼቲቩ ጎን እንዲቆሙም ጥሪ አቅርበዋል።

የአገራዊ ምክክር መድረኩ መክፈቻ በጥቅምት 2014 ዓ.ም እንዲሚሆነም ገልጸዋል።

ሁሉን አካታች አገራዊ የምክክር መድረክ የማመቻቸት ዓላማ ያለው ማይንድ ኢትዮጵያ በ2012 ዓ.ም የተመሰረተ የስምንት ድርጅቶች ጥምረት ነው።

የኢኒሼቲቩ አባላት ዴስቲኒ አትዮጵያ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፣ የሃሳብ ማዕድ፣  ጀስቲስ ፎር ኦል፣ ኢኒሼቲቪ ፎር ቼንጅ፣ የኢትዮጵያ እርቀ ሠላም ኮሚሽን፣ ኢትዮጵያን ፎር ኢንክሉሲቭ ዲያሎግ እና የሠላም ሚኒስቴር ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም