የጋዜጠኝነት ሙያና ሥነ-ምግባር በማያከብሩ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማትና ወኪሎች ላይ እርምጃ ይወሰዳል ... የመገናኛ ብዙሃን ባለሥልጣን - ኢዜአ አማርኛ
የጋዜጠኝነት ሙያና ሥነ-ምግባር በማያከብሩ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማትና ወኪሎች ላይ እርምጃ ይወሰዳል ... የመገናኛ ብዙሃን ባለሥልጣን
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 10/2013(ኢዜአ) የጋዜጠኝነት ሙያና ሥነ-ምግባር ሳይከተሉ በሚዘግቡ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማትና ወኪሎች ፍቃዳቸውን እስከመሰረዝ የሚያደርስ እርምጃ እንደሚወስድ የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ባለሥልጣን አሳሰበ።
የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር መሐመድ እድሪስ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፤ መንግሥት ለመገናኛ ብዙሃን የሰጠውን ነጻነት በአግባቡ ያለመጠቀም አዝማሚያ ታይቷል።
ለአንድ ወገን ያደላ፣ የአገርን ገጽታ የሚያጠለሽና ሐሰት መረጃ ላይ የተመሰረኮዘ የመገናኛ ብዙሃን ዘገባዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ጠቁመዋል።
"እንዲህ አይነት ከጋዜጠኝነት ሙያና ሥነ-ምግባር ያፈነገጡ ዘገባዎች በሂደት ይሻሻላሉ የሚል እምነት ቢኖርም በተቃራኒው የሐሰት ዘገባዎች ተባብሰዋል" ብለዋል።
በተለይም አሶሼትድ ፕሬስ በኢትዮጵያ ላይ የተዛቡ፣ ሚዛናቸውን የሳቱ፣ የአገሪቱን ሕግ የሚጥሱና ሐሰተኛ መረጃዎችን እያሰራጨ መሆኑን ገልጸዋል።
ተቋሙ በቅርቡም መጪውን ምርጫ በተመለከተ ላሰራጨው የሐሰት ዘገባ ማብራሪያ እንዲሰጥና በቀጣይ ተመሳሳይ ስህተት እንዳይሰራ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጠው ተናግረዋል።
በቅርብ ጊዜ አሶሼትድ ፕሬስ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ያለበትን የአቅም፣ የሎጂስቲክ አቅርቦት ችግርና አንዳንድ በዝግጅት ላይ ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ምክንያት ለተወሰኑ ጊዜያት ምርጫው እንዳራዘመ የተገለጸ ቢሆንም አሶሼትድ ፕሬስ ፍጹም ሃሰተኛ መረጃ ላይ የተነሳ ሪፖርት ማዘጋጀቱን ነው የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር የገለጹት።
ተቋሙ በሪፖርቱ ለምርጫ መራዘም እንደ ምክንያት ያልተጠቀሰ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከምርጫ መውጣታቸውና በትግራይ ላይ ያለው ችግርን እንደ ምክንያት ማቅረቡና ይህ ከጋዜጠኝነት ሥነ-ምግባርና ከሚዲያው ስታንዳርድ ጋር የሚቃረን መሆኑም ተጠቅሷል።
"አሶሼትድ ፕሬስ ከዚህ ቀደምም በነበሩ ዘገባዎች ሚዛኑን የጠበቀ ሪፖርት የማውጣት አዝማሚያ ስላልታየበት፤ ይህን ጉዳይ መረጃውን ከየት እንዳገኘው ማብራሪያ እንዲሰጥና ቀጣይ ሚዛኑን የጠበቀ እና ከሃሰተኛ መረጃዎች እንዲቆጠብ ማሳሰቢያ ሰጥተነዋል" ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ።
በተመሳሳይ ሌሎችም የመገናኛ ብዙሃን ተቋማትና ወኪሎች ከጋዜጠኝነት ሙያና ሥነ-ምግባር ያፈነገጡ ዘገባዎችን ከመሥራት እንዲቆጠቡ ጥሪ አቅርበዋል።
የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት የሚሰሯቸውን ዘገባዎች ትክክለኛነትና ሚዛናዊነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል አመቺ ሁኔታ ስላላቸው ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ በመጠየቅ፤ ከሙያው ሥነ-ምግባር ውጪ በሚንቀሰቀሱ ተቋማትና ወኪሎች ላይ ፍቃድ እስከ መዘሰረዝ የሚያደርስ እርምጃ እንደሚወሰድባቸው ነው ያረጋገጡት።
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ለ35 የውጭ መገናኛ ብዙኃን ተቋማት የሚሰሩ 129 ቋሚ የዜና ወኪል ፈቃድ የተሰጣቸው ጋዜጠኞች አሉ።
ከእነዚህም ውስጥ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት ኢትዮጵያዊ መሆናቸውን ባለሥልጣኑ ገልጿል።
ኢትዮጵያዊያን ጋዜጠኞች የሐሰት ዘገባዎች እንዲስተካከል በማድረግ ረገድ ያላቸው ተሳትፎ ዝቅተኛ መሆኑን የገለጹት አቶ መሐመድ ይህ ሊስተካከል ይገባልም ብለዋል።
በትግራይ ክልል የሚካሄደውን ሕግ ማስከበር ተከትሎ እስካሁን 64 የውጭ ጋዜጠኞች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ፈቃድ ተሰጥቷቸው እየዘገቡ መሆኑንም ገልጸዋል።