ቀጥታ፡

የውድድር አዘጋጅ ኮሚቴው የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በተሳሳተ መልኩ በመሰቀሉ ይቅርታ ጠየቀ

አዲስ አበባ ሃምሌ 26/2010 በ21ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ውድድር ላይ በ10 ሺህ ሜትር ወንዶች የሜዳሊያ ሽልማት አሰጣጥ ሥነ ስርዓት ላይ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በተሳሳተ ሁኔታ በመሰቀሉ የውድድሩ አዘጋጅ ኮሚቴ ይቅርታ ጠይቋል። ትናንት በናይጄሪያ አሳባ ከተማ በተካሄደው 10 ሺህ ሜትር የወንዶች ውድድር ጀማል ይመርና አንዱአምላክ በሪሁ አንደኛና ሁለተኛ በመውጣት የመጀመሪያውን የወርቅና የብር ሜዳሊያ ለአገራቸው አምጥተዋል። በሜዳሊያ ሽልማት አሰጣጥ ሥነ ስርዓቱ ላይ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ተገልብጦ በመሰቀሉ ለውድድር አዘጋጅ ኮሚቴው ጠንካራ ተቃውሞና አቤቱታ መቅረቡን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታውቋል። ሰንደቅ ዓላማው ከላይ አረንጓዴ፣ ከመሃል ቢጫ እና ከታች ቀይ ሆኖ መሰቀል ሲገባው ይህንን ሳይጠብቅ ቀዩ ከላይ ሆኖ በተሳሳተ ሁኔታ እንዲሰቀል መደረጉ ስህተት መሆኑን በመግለጽ ፌዴሬሽኑ ለኮሚቴው ቅሬታውን አቅርቧል። ሰንደቅ ዓላማው በትክክለኛው ቀለም ከላይ ወደታች አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ሆኖ በድጋሚ የማይሰቀል ከሆነ የልዑካን ቡድኑ ውድድሩን አቋርጦ ወደ አገሩ እንደሚመለስ ለውድድር አዘጋጅ ኮሚቴ ያሳወቀ መሆኑን ፌዴሬሽኑ ገልጿል። የውድድሩ አዘጋጅ ኮሚቴ የፌዴሬሽኑን ቅሬታ በመቀበል ለተፈጠረው ስህተት በይፋ ይቅርታ ጠይቆ በድጋሚ ሰንደቅ ዓላማው ተስተካክሎ መሰቀሉን ፌዴሬሽኑ አስታወቋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም