ቀጥታ፡

ዴሞክራሲ ምህዳሩን እያሰፋ የህዝቦችን ፍላጎት ማሟላት የሚችል "ሂደት" መሆኑን አንድ ጥናት አመለከተ

አዲስ አበባ ግንቦት 10/2013/ኢዜአ/ የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ በሂደት ምህዳሩን እያሰፋ የሚሄድና የህዝቦችን ፍላጎት ማሟላት የሚችል "ሂደት" መሆኑን አንድ ጥናት አመለከተ።

በሰላም ሚኒስቴር አዘጋጅነት “የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሽግግር ሂደት፣ ብሔራዊ መግባባት፣ ምርጫ 2013 እና ከዚያ ባሻገር” በሚል መሪ ሐሳብ ትናንት የተጀመረው ሃገራዊ የምክክር መድረክ በመካሄድ ላይ ይገኛል። 

በምክክር መድረኩ "የሽግግር ተሞክሮዎች ንጽጽራዊ ትንታኔ" የሚል ጥናታዊ ጽሑፍ በስትራቴጂ ጉዳዮች ተቋም ተመራማሪ ዶክተር ሄኖክ ጌታቸው ቀርቧል።

ዶክተር ሄኖክ በጽሑፋቸው እያንዳንዱ ሀገር የራሱ የሆነ የዴሞክራሲ ሽግግር ታሪክ እንዳለው ጠቅሰው ዴሞክራሲ ምህዳሩን እያሰፋ የሚሄድና የህዝቦችን ፍላጎት ማሟላት የሚችል "ሂደት" መሆኑን አብራርተዋል።

አንድ ሀገር የተሳካ የፖለቲካ ሽግግር እንዲያደርግ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የኃይማኖት ተቋማት፣ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች፣ የዴሞክራሲ ተቋማት፣ የሙያ እና ሠራተኛ ማህበራት፣ የህዝብ ተወካዮችና ሌሎች አካላት የራሳቸውን በጎ አስተዋጽኦ ማድረግ ይኖርባቸዋል ብለዋል።

በአንድ ሀገር የተሳካ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር እንዲደረግም ከውጫዊ ሁኔታ ይልቅ በውስጣዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሊደረግ ይገባል ነው ያሉት።

የተሳካ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ውጤታማ እንዲሆን መንግሥት ጠንካራ መሆን ይኖርበታል ሲሉም በፅሁፋቸው አመላክተዋል።

የምርጫ ተቋማትን ሪፎርም ማድረግ፣ የተፎካካሪ ኃይሎች ትብብር፣ ነጻና ገለልተኛ ሚዲያ ማቋቋምና ሌሎች የስኬታማ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር መገለጫ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

የእርስ በእርስ ግጭቶች፣ ሁከትና ግርግሮች መፈጠር ደግሞ ያልተሳካ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር መገለጫ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በሃገራዊ የምክክር መድረኩ የህዝብ ተወካይ ምክር ቤት አባላት፣ የኃይማኖት አባቶች፣ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የሚዲያ ባለሙያዎች እና የተለያዩ ምሑራን ተሳትፈዋል።

በሰላም ሚኒስቴር አዘጋጅነት እየተካሄደ ያለው ሃገራዊ የምክክር መድረክ ከግንቦት 9 እስከ 11 ቀን 2013 ዓ.ም ለተከታታይ ሦስት ቀናት የሚቆይ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም