ቀጥታ፡

ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር ጊዜና የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ይጠይቃል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 10/2013(ኢዜአ) ብሔራዊ መግባባት የመፍጠር ሂደት ጊዜ የሚፈልግና የበርካታ ባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ የሚጠይቅ በመሆኑ ተከታታይ ስራዎች እንደሚያስፈልጉ የሰላም ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል ገልጸዋል።

"የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሽግግር ሂደት፣ ብሔራዊ መግባባት፣ ምርጫ 2013 እና ከዚያ ባሻገር" በሚል መሪ ሀሳብ አገራዊ የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ ላይ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ የፖለቲካ ፖርቲዎች፣ የሲቪል ማህበራት፣ ምሁራን እና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የሰላም ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል እንደተናገሩት፣ ከምክክር መድረኩ ዓላማ አንዱ ባለፉት ሦስት ዓመታት የለውጡን ጉዞና የተገኙ ውጤቶችን መፈተሽ ነው።

በተጨማሪም የጋራ እሴቶችና ብሔራዊ ጥቅምን የሚያስጠብቁ ጉዳዮችን እንዴት ለአገር ግንባታ ሂደት ማዋል ይቻላል የሚሉ ሀሳቦች በመድረኩ እንደሚነሱ ገልፀዋል።

"ብሔራዊ መግባባት መፍጠርና እና የሰላም ባህልን የመገንባት ሂደት ጊዜ ይፈልጋል" ያሉት ሚኒስትሯ፣ የበርካታ ባለድርሻ አካላትን ተሳትፎና እያደገ የሚሄድ ሥራ መስራትን እንደሚጠይቅ ተናግረዋል።

እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ፤ ለሦስት ቀናት የሚቆየው አገራዊ የምክክር መድረክ ባለፉት ሦስት ዓመታት በታዩ ውጤቶችና ተግዳሮቶች ላይ ይመክራል።

የተስተዋሉ ክፍተቶችን በጋራ ለይቶ ለመሙላት፣ ቀጣይ የሥራ አቅጣጫዎች ላይ ግንዛቤ ለመያዝና የራስ ኃላፊነትን ለመውሰድ ጠቀሜታ እንዳለውም አመልክተው፤ በመድረኩ ሁሉም የዴሞክራሲ ተቋማት እንደሚሳተፉም ነው የገለጹት።

የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው አገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ መመካከር ብሔራዊ መግባባትን ለማጎልበት ያለው ጥቅም የጎላ መሆኑን ነው የገለጹት።

ተሳታፊዎቹ "ኢትዮጵያ ታስፈልገናለች ወይስ አታስፈልገንም?" በሚሉ ጉዳዮች ላይ ጠንከር ያለ ምክክር ማድረግና ጫፍ የወጡ አስተሳሰቦችን መመለስ እንደሚገባ ተናግረዋል።

በውይይቱ የሌሎች አገራትን ተሞክሮ ከእኛ አገር ጋር እንዴት አጣጥሞ መጓዝ ይቻላል የሚለውን ማየትና በቀጣይም የተሻለውን ማጠናከር እንደሚገባ ነው የተናገሩት።

ከግንቦት 9 እስከ 11 በሚካሄደው የምክክር መድረክ ከህዝቡ የተነሱ ጥያቄዎችን ጨምሮ ኢትዮጵያን በሽግግር ጎዳና፣ የሽግግር ተሞክሮዎች ንጽጽራዊ ትንታኔ፣ ጉዞ ወደ ብሔራዊ መግባባት፣ ተግዳሮቶችና መፃኢ እድሎች እንዲሁም ምርጫ 2013ን የሚዳስሱ የምክክር መነሻ ሀሳቦች ቀርበው ውይይት እንደሚካሄድባቸው ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም