ጠቅላይ ሚኒስትሩ የ2013 የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን በይፋ አስጀመሩ - ኢዜአ አማርኛ
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የ2013 የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን በይፋ አስጀመሩ
ግንቦት 10 ቀን 2013 (ኢዜአ) ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የ2013 የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን በይፋ አስጀመሩ።
"ኢትዮጵያን እናልብሳት" በሚል መርህ በሚካሄደው የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር 7 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል የታቀደ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 1 ቢሊዮን ችግኞች ለጎረቤት ሀገራት የሚቀርቡ መሆኑ ተገልጿል።
መርሃ ግብሩን በማስመልከት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከክልል ርእሳነ መስተዳድሮችና ሚኒስተሮች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርገዋል።
በውይይቱ ላይ እንዳነሱት፤ ለአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩ ስኬት ዜጎች ተሳትፏቸውን በማጠናከር "ኢትዮጵያን ለማልበስ" መዘጋጀት አለባቸው።
በዚህ መርሃ ግብር ኢትዮጵያ 6 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከልና 1 ቢሊዮን ችግኞችን ደግሞ ለጎረቤት ሀገራት ለማድረስ መዘጋጀቷን ገልጸዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በበኩላቸው የኢትዮጵያ የአረንጓደ አሻራ መርሃ ግብር አፍሪካን በልማት የማስተሳሰር አላማ እንዳለው አንስተዋል።
የአፍሪካን በጋራ የመልማት እቅድ ለማገዝ ኢትዮጵያ በሁሉም መስኮች የድርሻዋን በማበርከት ላይ መሆኗንም ገልጸዋል።
ለዚሁ መርሃ ግብር ስኬት ኢትዮጵያዊያን የተጠናከረ ተሳትፎ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።
በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከ25 ሚሊዮን በላይ ዜጎች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል።