አሶሺየትድ ፕሬስ ስለ ኢትዮጵያን ባሰራጨው የተሳሳተ ዘገባ ይቅርታ እንዲጠይቅ የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን አሳሰበ - ኢዜአ አማርኛ
አሶሺየትድ ፕሬስ ስለ ኢትዮጵያን ባሰራጨው የተሳሳተ ዘገባ ይቅርታ እንዲጠይቅ የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን አሳሰበ
ግንቦት 10 ቀን 2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ዘንድሮ የምታካሂደው ጠቅላላ ምርጫ መራዘም በማስመልከት አሶሺየትድ ፕሬስ በተሳሳተ መልኩ ሰሞኑን ባሰራጨው ዘገባ ይቅርታ እንዲጠይቅ የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን አሳሰበ።
ባለስልጣኑ ዛሬ በሰጠው መግለጫ አሶሺየትድ ፕሬስ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሪፎርም ሂደቱ የተገኘውን መልካም አጋጣሚ ከጋዜጠኝነትና ከስነ ምግባር ባፈነገጠ መልኩ በመጠቀም በኢትዮጵያ ላይ የተዛቡ፣ ሚዛናቸውን የሳቱ፣ የአገሪቱን ህግ የሚጥሱና ሀሰተኛ መረጃዎችን እያሰራጨ መሆኑን ገልጿል።
አሶሺየትድ ፕሬስ ግንቦት 7 ቀን 2013 ዓ.ም ያሰራጨው ዘገባ ከጋዜጠኝነት ሙያና ስነ ምግባር ያፈነገጠ አሉታዊ ድርጊት አይነተኛ ማሳያ መሆኑንም ባለስልጣኑ ጠቅሷል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በግልፅና በአደባባይ መድረክ ከሎጂስቲክ አቅርቦትና ከአጠቃላይ የስራ መጓተት ጋር ተያይዞ ምርጫው ላልተወሰኑ ሳምንታት እንዲራዘም ለሁሉም የፓለቲካ ፓርቲዎች ምክረ ሃሳብ ማቅርቡ ይታወቃል።
እውነታው ይህ ሆኖ እያለ፤ አሶሺየትድ ፕሬስ ፍፁም የተዛባና ትክክል ያልሆነ ዘገባ በጉዳዩ ላይ ማሰራጨቱን ባለስልጣኑ አስታውሷል።
በመሆኑም አሶሺየትድ ፕሬስ የሀሰተኛ መረጃ ምንጩን እንዲያሳውቅና ለተፈፀመው ጉልህ ስህተት ይቅርታ እንዲጠይቅ የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ጠይቋል።
አሶሺየትድ ፕሬስ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የሚሰራቸው ዘገባዎች በእውነት ላይ የተመረኮዙና ሚዛናቸውን የጠበቁ እንዲሆኑም ባለስልጣኑ አሳስቧል።