በዋሽንግተን ዲሲ እና አካባቢው የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በአለም ዓቀፍ ተቋማት እና አንዳንድ አገራት በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉትን ያልተገባ ተጽእኖ ተቃወሙ - ኢዜአ አማርኛ
በዋሽንግተን ዲሲ እና አካባቢው የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በአለም ዓቀፍ ተቋማት እና አንዳንድ አገራት በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉትን ያልተገባ ተጽእኖ ተቃወሙ
ግንቦት 10 ቀን 2013 (ኢዜአ) በዋሽንግተን ዲሲ እና አካባቢው የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በአለም ዓቀፍ ተቋማት እና አንዳንድ አገራት በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉትን ያልተገባ ተጽእኖ በመቃወም ትናንት በዋሽግተን ዲሲ ሰላማዊ ሰልፍ አካሂደዋል።
በሰልፉ ላይ የኢትዮጵያ በሚደረግባት ጫና እንደማትንበረከክና አሸናፊ ሆና የምትወጣ መሆኗን የሚገልጹ መፈክሮች ተነግረዋል።
“ኢትዮጵያ ሉዓላዊ አገር ነች፤ በአንድነት ስንቆም የውስጥም የውጭም ሃይሎችን እናሸንፋለን፤ ከጽንፈኞች ጋር ድርድር አይደረግም፤ ቀጣዩ ምርጫ በሰላም እንዲጠናቀቅ እንደግፋለን፣ ለኢትዮጵያ ችግሮች መፍትሄዎቹ ኢትዮጵያውያን ናቸው፣ የህዳሴ ግድቡን እንሞላዋለን” የሚሉ መፈክሮች በሰልፈኞቹ ተነግረዋል።
“የግዛት አንድነቷን ለማስጠበቅና ጠላቶቿን ለመመከት የምትወስደውን እርምጃ የሚወሰነው በኢትዮጵያ መንግስት እንጂ ከሌላ አገር በሚመጣ መግለጫ ወይም መመሪያ አይደለም’ ሲሉም ሰልፈኞቹ ድምጻቸውን አሰምተዋል።
ሰልፈኞቹ አንዳንድ አገራት በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉትን ያልተገባ ጫና እንዲያቆሙ እና በአሸባሪው ህወሃት ደጋፊዎች የሚነዛውን የሃሰት ፕሮፖጋንዳ ተመርኩዘው በየጊዜው ከሚያወጡት የተዛባ መግለጫ እንዲቆጠቡ ጠይቀዋል።
በተለይም ክትናንት በስቲያ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በኢትዮጵያ ላይ ያወጣው መግለጫ የአገራቱን የቆዬ ወዳጅነት ያላገናዘበ፣ በሃሰት መረጃዎች ግፊት የወጣ እና ለኢትዮጵያ ሰላም እና ሉዓላዊ አንድነት የማይጠቅም እንደሆነ ገልጸዋል።
አሜሪካ እና አለም ዓቀፉ ማህበረሰብ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድርድር በፍትሃዊነት እንዲቋጭ ግብጽ ከያዘችው ግትር አቋም እና የሃሰት ፕሮፖጋንዳ ወጥታ ለጋራ ተጠቃሚነት እንድትሰራ ግፊት እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።
ቀጣዩ አገራዊ ምርጫ በሰላም እንዲጠናቀቅ እና ኢትዮጵያ የገጠሟትን ፈተናዎች በድል እንደትሻገር ከምንጊዜውም በላይ አበክረው እንደሚሰሩም የሰልፉ ተሳታፊዎች ገልጸዋል።