ቀጥታ፡

ለዜጎች የሚሰጠው አገልግሎት ውጤታማና ቀልጣፋ ባለመሆኑ መዋቅራዊ ችግር ማስከተሉ ተገለጸ

ግንቦት 9/2013 (ኢዜአ) በመንግስት ተቋማት ለዜጎች የሚሰጠው አገልግሎት ውጤታማና ቀልጣፋ በሆነ መንገድ ተደራሽ ባለመደረጉ መዋቅራዊ ችግር ማስከተሉን የሠላም ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስቴሩ ከፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ጋር በመተባበር "ብሔራዊ የመንግስት አገልግሎት ዘርፍ ተኮር የምክክር መድረክ" በቢሾፍቱና አዳማ ከተሞች ለሦስት ቀናት አካሂዷል።

በመድረኮቹ ከትግራይ ክልልና ከአዲስ አበባ አስተዳደር ከቢሮ እስከ ወረዳ ጽህፈት ቤት ድረስ ያሉ የሪፎርምና መልካም አስተዳደር ኃላፊዎችና የፌዴራል ተቋማት የሲቪል ሰርቪስ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።

የሠላም ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል በምክክሩ ማጠቃለያ መንግስት ለዜጎች የሚሰጠው አገልግሎት በፈጻሚ አካላት በኩል ቀልጣፋና ውጤታማ በሆነ መንገድ ተደራሽ ባለመሆኑ የሠላም ችግር መንስዔ ሆኗል ብለዋል።

በአገሪቱ ዘላቂ ሠላም ለማስፈን መንግስት ለዜጎች የሚሰጠውን አገልግሎት ዜጋ ተኮር አድርጎ መስራት እንደሚገባም አብራርተዋል።

"በየደረጃው ያሉ የመንግስት ተቋማት የሚሰጡት አገልግሎትና ምላሽ አሰጣጥ ተግባራት ጥራት እየተጓደለ በሄደ ቁጥር ከሕዝብ ጋር ያለው ግንኙነት እየሻከረ ይሄዳል" ነው ያሉት ሚኒስትሯ።

እንደ እርሳቸው ገለጻ ለሕዝብ የሚሰጡት አገልግሎት እየተጓደለ በሄደ ቁጥር በመንግስትና በሕዝብ መካከል ያለው ግንኙነት እየሻከረ ይሄዳል።

የዜጎች በመንግስት ላይ ያላቸው እምነት መሸርሸር በቀላሉ የሚታይ አይደለም ያሉት ወይዘሮ ሙፈሪያት እምነት ኖሯቸው ለአገረ መንግስት ግንባታ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት ይገባል ብለዋል።

በተለይ በአስተሳሰብ፣ በአደረጃጀትና በአሰራር ላይ ባህሪያዊ ለውጥ ማምጣት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ማተኮር እንደሚገባ አመልክተዋል።

ለሠራተኞች ቅድሚያና አክብሮት የሚሰጥ አመራር መገንባት እንዳለበት የገለጹት ሚኒስትሯ ሠራተኞችም ለሚያገለግሉት ዜጋ አክብሮት ያለው አገልግሎት መስጠት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

በመድረኮቹ የኢትዮጵያ የሠላም ፖሊሲ ዕይታና ብሔራዊ ምክክር፣ ማኅበራዊ ሀብቶቻችን ለሠላም ግንባታ፣ የሕግ የበላይነትና የዜጎች ክብር፣ በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የመልካም አስተዳደር ተግዳሮቶችና የወደፊት ዕድሎች ላይ በባለሙያዎች ገለጻ ተደርጓል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም