ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በአባይ ውሀ ላይ ያላት አቋም የጋራ ተጠቃሚነት የሚያረጋገጥ መሆኑን ምሁራን ተናገሩ

ጅማ፤ ግንቦት 9/2013(ኢዜአ ) ኢትዮጵያ በአባይ ውሀ ላይ የያዘችው አቋም የጋራ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥና የህግ ድጋፍ ያላት መሆኑን ምሁራን ተናገሩ።

"የዩኒቨርሲቲዎች ትብብር በአባይ"  በሚል ርዕስ የተዘጋጀ  የምሁራን የውይይት መድረክ በጅማ ዩኒቨርሲቲ ተካሂዷል፡፡

የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ጀማል አባ ፊጣ የውይይት መድረኩን ሲከፍቱ ፤የኢትዮጵያ አቋም የጋራ ተጠቃሚነት ሲሆን ግብጽ የግል ንብረቷ በማስመሰል ትከራከራለች ብለዋል፡፡

በተዛባ ትርክትና ፍትሀዊ ባልሆነ የቅኝ ግዛት ሰነዶችን በማጣቀስ ውሃውን አትንኩብኝ በማለት እስከ ማስፈራራት መድረሷ በምንም አግባብ ተቀባይነት አይኖረውም ሲሉም ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብቷ የመጠቀም መብትና የህግ ድጋፍ ያላት መሆኑን ለዜጎች ሁሉ ማሳወቅ የሚገባ በመሆኑ ምሁራን በጉዳዩ ዙሪያ ሰፋ ያለ ትንታኔ መስጠት እንዲችሉ የተዘጋጀ መድረክ መሆኑን አስታውቀዋል።

የአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ  መምህር ዶክተር ያቆብ ኤርሳሞ  በቀረቡት የመነሻ ጽሑፍ "የኢትዮጵያ አቋም በአባይ ወንዝ እና ልማት ላይ እኛም  እናንተም ተጠቀሙ የሚል ሲሆን በተቃራኒው ግብጽ የአባይን ውሃ አትንኩ፤ ከነካችሁም እኛን አሳውቃችሁ መሆን አለበት የሚል ነው " ብለዋል፡፡

የግብጽም ሆነ የሱዳን ፍላጎት ምንም ዓይነት የውሃ ሙሌት ያለነሱ ፍቃድ እንዳይካሄድ መሆኑን ፤ ኢትዮጵያ በበኩሏ በጉዳዩ ዙሪያ ያላትን የጸና ጽኑ አቋም  በመግለጽ ላይ እንደምትገኝ አስረድተዋል፡፡

ዶክተር ኢንጅነር ይልማ ስለሺ ባቀረቡት ጽሁፍ  የግብጽ ክስ እኛ ውሃ የለንም የሚል ሲሆን ግብጽ  ያላትን 154 ትሪሊየን ሜትር ኪዩብ የከርሰ ምድር ውሃ አውጥታ ብትጠቀም 50 ዓመት የውሃ ፍጆታ ይኖራታልም ብለዋል፡፡

ግብጽ አስዋን ጨምሮ ሌሎችም ታላላቅ ግድቦች እንዳላት ዶክተር ኢንጅነር ይልማ በጽሑፋቸው ጠቅሰዋል፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ክፍሌ ሆሮ በበኩላቸው፤ የህዳሴው ግድብ ፕሮጀክት 80 በመቶ መጠናቀቁን ተናግረዋል፡፡

የሁለቱን ተርባይን ጀነሬተሮች በመጠቀም ሀይል ማመንጨት የሚያስችል ዝግጅት ተደርጓል፤ ፕሮጀክቱ የተሻለ አፈጻጸም ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በራስዋ ሀብት የመጠቀም መብት እንዳላት ማሳየት ያስፈልጋል ያሉት ኢንጅነር ክፍሌ፣ ለልማቷ መፋጠንና ለዜጎቿ ተጠቃሚነት ግድቡ ወሳኝ ድርሻ ያለው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም