የፖለቲካ ፓርቲዎች በኢኮኖሚ ዘርፍ የክርክር መድረክ አካሄዱ - ኢዜአ አማርኛ
የፖለቲካ ፓርቲዎች በኢኮኖሚ ዘርፍ የክርክር መድረክ አካሄዱ
ደብረ ብርሃን ፤ ግንቦት 9/2013(ኢዜአ) በስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የሚወዳደሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በኢኮኖሚው ዘርፍ ባላቸው ፖሊሲ ዙሪያ በደብረብርሃን ከተማ የክርክር መድረክ አካሄዱ።
ኢንተር አፍሪካ ግሩፕ ባዘጋጀው የክርክር መድረክ ብልጽግና ፣ ኢዜማና እናት ፓርቲዎች ተሳትፈዋል።
የብልጽግና ፓርቲን ወክለው በክርክሩ የተሳተፉት አቶ ግርማ የሺጥላ እንዳሉት፤ በኢኮኖሚው ዘርፍ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን ለመፍታት ፓርቲያቸው ፖሊሲ ቀርፆ እየሰራ ነው።
ሃገሪቱ አሁን ካለችበት ችግር ለማውጣት ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ምንጮችን በመጠቀም ፓርቲያቸው እንደሚሰራ ገልጸዋል።
የተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚ ግንባታ ላይ እንደሚሰራ ጠቅሰው፤ የግል ባለሀብቶችን በማበረታታት ለሀገር ግንባታና ለዜጎች ሁለንተናዊ ጥቅም ፓርቲው ቁርጠኛ አቋም እንዳለው አመልክተዋል።
ብልጽግና የህዝብን አዎንታ አግኝቶ በስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ከተመረጠ ልማትን ለማፋጠን በሚችሉ በመንገድ፣ ጤና፣ ትምህርት፣ኢንቨስትመንትና ሌሎችም ዘርፎች ለመስራት መዘጋጀቱን አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ/ኢዜማ/ የብሄራዊ ፖሊሲ ዝግጅት አስተባባሪ አቶ አማን ይሁን ረዳ በበኩላቸው የሃገሪቱ የኢኮኖሚ ችግሮች እንዲፈቱ ለማስቻልም ህዝቡን በአነስተኛ የወለድ መጠን የብድር አገልግሎት ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
የተረጋጋ ማይክሮ ኢኮኖሚ ለመፍጠር የኑሮ ውድነትንና የዜጎችን የስራ እጥነት ችግር ለመፍታት በገጠርም ሆነ በከተማ የትራንስፖርትና የመኖሪያ ቤት እጥረትን ለመፍታት ፓርቲያቸው እንደሚሰራም አስታውቀዋል።
የሀገር ውስጥና ውጭ ባለሀብቶችን በስፋት በማሳተፍ ተወዳዳሪ የገበያ ስርዓት በመዘርጋት አምራችና ሸማቹን በማቀራረብ የኑሮ ውድነቱን ለመቀነስ የሚሰራውን ፓርቲያቸው በፖሊሲው ማካተቱን ጠቅሰዋል።
የእናት ፓርቲ ተወካይ አቶ ጌታቸው አስፋው እንደተናገሩት፤ ፓርቲያቸው ቢመረጥ ቅይጥ ኢኮኖሚን ይከተላል።
ሀገር በቀል እውቀትን መሰረት በማድረግ አሁን የሚስተዋሉትን የኢኮኖሚ ችግሮች የሚፈታ ፖሊሲ ቀርፆ ለምርጫው ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።
ፓርቲያቸው ከተደራጀ በአጭር ግዜ ውስጥ ለህዝብ ተወካዮችና ክልል ምክር ቤቶች የሚወዳደሩ ከ500 በላይ ዕጩዎችን ማቅረቡንም ጠቅሰዋል።
ኢንተር አፍሪካ ግሩፕ ያዘጋጀው የክርክር መድረክ መራጩ ህዝብ የራሱን ውሳኔ እንዲሰጥ የሚያስችል ግልጽና ተከራካሪ ፓርቲዎችም ሃሳባቸውን በነፃነት ለህዝብ የሸጡበት እንደሆነም ተናግረዋል።
የኢንተር አፍሪካ ግሩፕ ስራ አስኪያጅ አቶ ታምራት ከበደ ኢንተር አፍሪካ ግሩፕ ዴሞክራሲን ከማጎልበትና በሰላም ግንባታ ሂደቶች ሲሰራ መቆየቱን አመልክተዋል።
የክርክር መድረኩ የተዘጋጀው ፓርቲዎች በኢኮኖሚ ዘርፍ የያዟቸው ፖሊሲዎች ለህዝብ ለማስተዋወቅ በመረጡት መሰረት መሆኑን ገልጸዋል።
ለመከራከር የቀረቡት የፓርቲ አባላት በመከባበር በሚቀርብላቸው ጥያቄዎች ላይ ተገቢውን መልስ ከመስጠት ባለፈ እንደከዚህ ቀደሙ መዘላለፍ የሌለበት ነው ብለዋል።
የኢንተር አፍሪካ ግሩፕ በተመሳሳይም በቀጣይ በሀዋሳና በሱማሌ ክልል ተመሳሳይ መድረክ ለማካሄድ ማቀዱንም ጠቁመዋል።