በድሬዳዋ በክረምት ወቅት በአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ከ2 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ ነው- ባለስለጣኑ - ኢዜአ አማርኛ
በድሬዳዋ በክረምት ወቅት በአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ከ2 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ ነው- ባለስለጣኑ
ድሬዳዋ ግንቦት 9/2013 (ኢዜአ) በድሬዳዋ በክረምት ወቅት በአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ከ2 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የአስተዳደሩ የአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን አስታወቀ።
በባለስልጣኑ የደን ልማት ቡድን መሪ አቶ ማሙሽ ዘውዱ ለኢዜአ እንዳስታወቁት በዘንድሮ ክረምት በ3ተኛው የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር የሚተከሉ ከ2 ሚሊዮን በላይ ችግኞች እየተዘጋጁ ነው።
በአስተዳደሩበገጠርና በከተማ ለሚካሄደው ተከላ በ16 ጣቢያዎች ችግኞች የማፍላት ስራ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።
እየተዘጋጁ ካሉት ችግኞች ውስጥ1 ነጥብ 4 ሚሊዮኑ በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ፣ በጽዳትና ውበትና በምግብ ዋስትና ኤጀንሲዎችአማካኝነት የሚተከሉ መሆናቸውን አመልክተዋል።
ለተከላ እየተዘጋጁ ያሉት ችግኞች ለጥላ ዛፍ፣ ለጥምር ደን ልማትና ለፍራፍሬ ምግብነት የሚያገለግሉ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በክረምት ወቅት የችግኝ ተከላውን ስኬታማ ለማድረግ ከድሬዳዋ ግብርና ቢሮ ጋር በተቀናጀ መንገድ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በአስተዳደሩ አምና ከተተከሉ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ችግኞች ውስጥ 68 በመቶ መጽደቃቸውን ቡድን መሪው አስታውቀዋል።
በዋና ዋና ጎዳና ላይ ለሚተከሉ የጥላ ዛፎች ህብረተሰቡ የሚያደርገውን ጥበቃ አጠናክሮ እንዲቀጥልጠይቀዋል።
እንደ አቶ ማሙሽ ማብራሪያ ዘንድሮ ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት ለምታደርገው ዘርፈ ብዙ ጥረት ወሳኝ በሆነው የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ ላይ የጎረቤት ሀገሮች እንዲሳተፉ ጥራታቸውን የጠበቁ ችግኞች ታቀርባለች፡፡
"በተለይ በሀገሪቱ ጠረፋማ አካባቢዎች የሚገኙ የድሬዳዋ ከተማ፣ኦሮሚያ፣ የአማራና የሶማሌ ክልሎች ለሚጎራበቷቸው ሀገሮች ችግኞች ያቀርባሉ" ብለዋል፡፡
ድሬዳዋም ችግኞችን ለጅቡቲ ለማቅረብ ከፌደራል መንግስት በተመደበ 5 ሚሊዮን ብር የችግኝ ማፍላት ሥራ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አሁን ላይየሁለት ትላልቅ ሼዶች ግንባታ፣ የችግኝ አልጋዎች ስራና የቁሳቁስና አፈር አቅርቦት ተጠናቆ በቤተ-ሙከራ የታገዘ የችግኝ ማፍላት ስራ ለመጀመር ዝግጅት መጠናቀቁን አመልክተዋል።
የድሬዳዋ ግብርና፣ ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ በበኩላቸው በክረምት ለሚካሄደው የችግኝ ተከላ ከበጋ ወቅት የተፋሰስ ልማት ስራ በተጓዳኝ የጉድጓድ ቁፋሮ መካሄዱን ተናግረዋል።
በቢሮው በኩል 600ሺህ ችግኞች ለመትከል ቢታቀድም ከ1 ሚሊዮን በላይ ችግኞች መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል።