ክልሎች በመራጮች ምዝገባና ቅስቀሳ ሂደት የጎላ የጸጥታ ችግር እንዳላጋጠማቸው ተገለፀ - ኢዜአ አማርኛ
ክልሎች በመራጮች ምዝገባና ቅስቀሳ ሂደት የጎላ የጸጥታ ችግር እንዳላጋጠማቸው ተገለፀ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9/2013/ኢዜአ/ በ6ኛው አገራዊ ምርጫ የምረጡኝ ቅስቀሳና የመራጮች ምዝገባ ሂደቶች የጎላ የጸጥታ ችግር እንዳላጋጠማቸው የክልሎች የሠላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊዎች ገለጹ።
ኢትዮጵያ በዚህ ዓመት ለምታካሂደው ጠቅላላ ምርጫ በፓርቲዎች የምረጡኝ ቅስቀሳ፣ በመራጮች ምዝገባና ተጓዳኝ ሁነቶች ክንውኖች ላይ ትገኛለች።
የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችና የአማራ ክልሎች የሠላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊዎች ለኢዜአ እንደገለጹትም የቅድመ ምርጫ ሂደቱ ሠላማዊ ነው።
በደቡብ ክልል የወላይታ ዞን ሠላምና ጸጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ጉአ በእስካሁኑ የምርጫ ሂደት የጎላ ችግር አለማጋጠሙን በቀጣይም የጸጥታ ችግር እንዳያጋጥም ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።
በክልሉ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመልካም አስተዳደር ዘርፍ አስተባባሪና የሠላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ዓለማየሁ ባውዲ በበኩላቸው ዜጎች ያለምንም የጸጥታ ችግር በነጻነት እንዲመርጡ ዝግጅት ተደርጓል ነው ያሉት።
በክልሉ በሶስት ዞኖች 8 ምርጫ ጣቢያዎች ያለውን የጸጥታ ሁኔታ በመገምገም ምርጫ ማካሄድ እንደማይቻል በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መገለጹንም ተናግረዋል።
እንደ ኃላፊው ገለጻ የምርጫውን ደህንነት ለማረጋገጥ ከ24 ሺህ በላይ ሚሊሻዎች የተመለመሉ ሲሆን ከ10 ሺህ በላይ መደበኛ ፖሊስና በ11 ሻለቃዎች የተከፋፈለ ልዩ ኃይል ተዘጋጅቷል።
የአማራ ክልል ሠላምና የሕዝብ ደህንነት ጉዳዮች ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ እንግዳው ጠገናውም የጸጥታ ኃይሉ የምርጫውን ሠላማዊነት ለማደፍረስ የሚሰሩ ኃይሎችን በኅብረተሰቡ ትብብር ለማጋለጥ እየሰራ ነው ብለዋል።
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የ6ኛውን አጠቃላይ ምርጫ ድምጽ መስጫ ግንቦት 28 እና ሰኔ 5 ለማካሄድ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም መራዘሙንና በሁሉም የአገሪቷ አካባቢዎችም በአንድ ቀን እንደሚካሄድ መወሰኑን መግለጹ ይታወቃል።