የሸሪዓ ፍርድ ቤቶችን ሚና ማጠናከር ለሀገር የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የሸሪዓ ፍርድ ቤቶችን ሚና ማጠናከር ለሀገር የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9/2013 ( ኢዜአ) የሸሪዓ ፍርድ ቤቶችን ማጠናከር ለሀገር የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ወሳኝ መሆኑን የፍትሕ፣ ሕግ ምርምርና ስልጠና ኢንስቲትዩት ገለጸ።
ኢንስቲትዩቱ ለሸሪዓ ፍርድ ቤት ዳኞች የአቅም ግንባታ ስልጠና መስጠት ጀምሯል።
የፍትሕ፣ ሕግ ምርምርና ስልጠና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ደግፌ ቡላ ለፌዴራልና ክልል ሸሪዓ ፍርድ ቤት ዳኞች የተዘጋጀውን የስልጠና መርሃ ግብር ከፍተዋል።
በዚሁ ጊዜ ባደረጉት ንግግርም በሕገ መንግስቱ እውቅና ከተሰጣቸው ሃይማኖታዊ የፍትሕ ተቋማት መካከል በእስልምና ሃይማኖት የሚተገበረው የሸሪዓ ፍርድ ቤት አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ከመደበኛ ፍርድ ቤቶች በተጨማሪ ሰፊ ህዝብ ለሚገለገልበት የሸሪዓ ፍርድ ቤት የዳኝነት አገልግሎት እምብዛም ትኩረት ሳይሰጠው መቆየቱንም አስታውሰዋል።
በዚህም ኢንስቲትዩቱ ለሸሪዓ ፍርድ ቤት ዳኞች የአቅም ግንባታ ስልጠና ማዘጋጀቱን አንስተው፤ ስልጠናው በዋናነት በሸሪአ ሕግ፣ በሴቶችና ህጻናት መብቶች ጥበቃና በፍትሃ ብሔር ጉዳዮች ላይ ያተኮረ መሆኑን ገልፀዋል።
የሸሪአ ፍርድ ቤት ዳኞች ስልጠናውን ከወሰዱ በኋላ ለህብረተሰቡ የተፋጠነ ፍትህ እንዲሰጡ ለማስቻል ያለመ መሆኑንም ነው ዋና ዳይሬክተሩ ያስረዱት።
ይህም የደንበኞችን የፍትህ አገልግሎት ለማሻሻልና የዳኞችን የዳኝነት አሰጣጥ አቅም ለማጎልበት ጉልህ ሚና እንደሚኖረው አንስተዋል።
የሸሪአ ፍርድ ቤቶች ውጤታማ ሥራ ከሰሩ የአገር ሰላምን ለማረጋገጥ፣ የዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ለማጠናከርና የፍርድ ቤቶችን አቅም ለመገንባት ወሳኝ ሚና እንደሚኖረውም ገልጸዋል።
የሸሪዓ ፍርድ ቤት ተደራሽ የፍትሕ አገልግሎት በመስጠት ለሰላምና ልማት ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ጠቁመው፤ በቀጣይም በኢንስቲትዩቱ በኩል የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች እንደሚሰጡ አረጋግጠዋል።

የፌዴራል ጠቅላይ ሸሪዓ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ሸህ መሃመድ አልሙባረክ ሸኽ ሙሀመድ አወል በበኩላቸው ስልጠናው በሸሪዓ ፍርድ ቤት የሚታዩ አንዳንድ ጉዳዮች ከዘመኑ ዕድገትና ቴክኖሎጂ ጋር ስለመያያዛቸው ግንዛቤ ለመፍጠር እንደሚያግዝ ገልጸዋል።
ከዚህ በፊት ከውጭ አሰልጣኝ በማምጣት ለዳኞች ስልጠና ሲሰጥ እንደነበር አስታውሰው፤ በአሁኑ ወቅት በኢንስቲትዩቱ ስልጠናው መሰጠት መጀመሩ ትልቅ ዕድል መሆኑን ገልጸዋል።
የሸሪዓ ፍርድ ቤት የፍትህ ስርአት የሙስሊሙ ህብረተሰብ የሚዳኝበት በሕግ ዕውቅና የተሰጠው የዳኝንት አገልግሎት ቢሆንም አልፎ አልፎ በአንዳንድ ሰዎች ያለመቀበል አዝማሚያዎች እንዳሉ ገልጸው፤ ይህም መስተካከል እንዳለበት ጠቁመዋል።
ሰልጣኝ ዳኞችም ከስልጠናው መልስ ያገኙትን እውቀትና ግንዛቤ በተግባር ላይ በማዋል የተሻለ የዳኝነት አገልግሎት መስጠት እንዳለባቸው ነው ፕሬዚዳንቱ የተናገሩት።