ቀጥታ፡

የቤተክርስቲያኗ አባቶች ምዕመኑ ከተፈጠረው ሰላም ትምህርት ወስዶ በፍቅርና በአንድነት ለአገሩ እንዲሰራ ጠየቁ

አዲስ አበባ ሀምሌ 26/2010 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ምዕመን አሁን በአባቶች መካከል ከተፈጠረው እርቀ ሰላም ትምህርት ወስዶ በፍቅርና በአንድነት ለአገሩ መስራት እንዳለበት የቤተክርስቲያኗ አባቶች ጠየቁ። በሲኖዶሱ የተፈጠረው እርቀ ሰላም በኢትዮጵያውያን መካከል አንድነት እንዲፈጠር ትልቅ ፋይዳ እንዳለውም አክለዋል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ለ1ሺህ650 ዓመታት ከግብጽ በሚላክላት ጳጳስ ስትመራ የቆየች ሲሆን፤ በ1951 ዓ.ም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስሊዮስ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ጳጳስ በመሆን ቤተክርስቲያኒቱን እንዳገለገሉ የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ። ይሁንና ቤተክርስቲያኒቱ ላለፉት ሁለት አስርት የውጭና የአገር ውስጥ ሲኖዶስ በሚል ተከፋፍላ ቆይታለች። በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በተገኙበት በሰሜን አሜሪካ በተካሄደው እርቀ ሰላም ሁለቱ ሲኖዶሶች ወደ አንድ መምጣታቸውን ተከትሎ ብጽወ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዎስ ከዓመታት በኋላ ትናንት ወደ አገራቸው ገብተዋል። በዕለቱም የቤተክርስቲያኒቱ አባቶችና ምዕመናን ለብፅዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዎስ እና ብጹዓን አባቶች በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ደማቅ አቀባባል አድርገውላቸዋል። ይህን እርቀ ሰላም አስመልክቶ ኢዜአ ያነጋጋራቸው አባቶች እንዳሉት፤ ህዝበ ክርስቲያኑ ከዚህ ተምሮ በፍቅርና በአንድነት አገሩን ማገልገል አለበት። አባ መላዕከ ሰላም ሰለሞን የተፈጠረው ሰላም ትልቅ ነጸብራቅ ስለሆነ ወደፊት ምዕመኑ ይህን ፍቅርና አንድነት አጽንቶ ለአገሩ እድገት መስራት እንዳለበት ተናግረዋል። ህዝበ ክርስቲያኑ አንድ በመሆን ከቤተክርስቲያኒቱ መሪዎች ጋር በመሆን ለአገር ታላቅነት መሰራት እንዳለበት የተናገሩት ደግሞ ሊቀጠበብት ደምሴ ስመኝ ናቸው። በቤተክርስቲያኒቱ የተፈጠረው አንድነትም ለህዝቦች መፈቃቀርና ህብረት ትልቅ ፋይዳ አለው ነው ያሉት። አባ እስጢፋኖስ ምህረቱ በበኩላቸው ሰላም ባልነበረበት ጊዜ ቤተክርስቲያኒቱ ተከፋፍላ መቆየቷን ገልጸው፤ ምዕመኑ ይህን ሰላምና አንድነት እንዳይደፈርስ መስራት እንዳለበት አውስተዋል። በቤተክርስቲያኒቱ ሰላምና አንድነት ካለ እጅ ለእጅ ተያይዞ ለአገር እድገት መስራት ቀላል እንደሚሆን ተናግረዋል። መምህር በትረ ጥዑመልሳን በበኩላቸው ህዝበ ክርስቲያኑ ዘረኝነትና መከፋፋልን በማስወገድ ሰላምን መስበክ እንደሚያስፈለግ ገልጸዋል። በቤተክስቲያኗ ምዕመን ዘንድ አንድነትን በማጠናከር ለቤተክርስቲያኗ እና ለአገር በመስራት አሁን የተገኘውን ጸጋና በረከት ሁሉም እንዲያስቀጥል ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም