ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማቋቋም እየተሰራ ነው ---ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሚሊዮን ማቲያስ

73
ሃዋሳ ሀምሌ26/2010 በደቡብ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች ተፈጥሮ በነበረው ግጭት የተፈናቀሉ ዜጎችን በዘላቂነት ለማቋቋም እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አስታወቁ፡፡ የወጋገን ባንክ ከምዕራብና ምስራቅ ጉጂ ዞኖች የተፈናቀሉ ወገኖችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ ለሚከናወነው ተግባር ማስፈጸሚያ የሚውል 5 ሚሊዮን ብር በድጋፍ ሰጥቷል፡፡ ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ሚሊዮን ማቲያስ በወቅቱ እንደገለፁት በክልሉ ውስጥና ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብና ምስራቅ ጉጂ ዞኖች አዋሳኝ አካባቢዎች ተፈጥረው በነበሩ ግጭቶች በርካታ ዜጎች ተፈናቅለዋል ። ተፈናቃዮቹ በጌዴኦ፣ አማሮ፣ ቡርጂና ሀዋሳ አካባቢዎች በመጠለያ ጣቢያዎች ሰፍረው እንደሚገኙ አስታውሰዋል፡፡ ከፌደራል መንግስትና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ችግሮችን በጋራ በመፍታት ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማቋቋም እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል። ተፈናቃዮችን እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2010 ዓ.ም ወደቀያቸው ለመመለስና መደበኛ ኑሯቸውን እንዲቀጥሉ ለማድረግም በክልሉ የገቢ አሰባሳቢ ኮሚቴ ተዋቅሮ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል። የወጋገን ባንክም 5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ በማድረግ ላሳየው አጋርነትም አቶ ሚሊዮን  ምስጋና አቅርበዋል ። የወጋገን ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ወንድይፍራው ታደሰ በበኩላቸው እንዳሉት ለወገን ደራሽ ወገን ነው በሚል እሳቤ በተለያዩ ጊዜያት በተከሰቱ ግጭቶች የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመደገፍ  ባንኩ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም