የአዋላጅ ነርሶችን ቁጥርና ብቃት በማሳደግ የእናቶችንና ሕፃናትን ሞት ትርጉም ባለው መልኩ መቀነስ ይገባል...ማህበሩ - ኢዜአ አማርኛ
የአዋላጅ ነርሶችን ቁጥርና ብቃት በማሳደግ የእናቶችንና ሕፃናትን ሞት ትርጉም ባለው መልኩ መቀነስ ይገባል...ማህበሩ
ሀዋሳ፤ግንቦት 8/2013 (ኢዜአ) በሀገሪቱ የአዋላጅ ነርሶችን ቁጥርና ብቃት በማሳደግ የእናቶችንና ሕፃናትን ሞት ትርጉም ባለው መልኩ መቀነስ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሚድዋይፈሮች ማህበር አስታወቀ።
“መረጃው ግልፅ ነው ትኩረት ለሚድዋይፈሮች ” በሚል መሪ ቃል 29ኛው ዓለም አቀፉ የሚድዋይፈሮች ቀን በደቡብና ሲዳማ ክልሎች የሚድዋይፈሮች ማህበር የጣምራ ዝግጅት በሀዋሳ ከተማ ተከብሯል ፡፡
የኢትዮጵያ ሚድዋይፈሮች ማህበር ምክትል ፕሬዝዳንት ረዳት ፕሮፌሰር ሰለሞን ኃይለመስቀል በወቅቱ እንደተናገሩት በዓለም አቀፍ ደረጃ የጤና ባለሙያዎች እጥረት እየተስተዋለ ነው።
የባለሙያ እጥረቱ በኢትዮጵያ የጎላ መሆኑን ያመለከቱት ምክትል ፕሬዝዳንቱ በተለይ የእናቶችና ሕፃናትን ሞት ትርጉም ባለው መልኩ ለመቀነስ እንዲቻል አዋላጅ ነርሶችን በቁጥርና በብቃት ማሳደግ እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል።
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ካሉ 17 ሺህ የሚጠጉ አዋላጅ ነርሶች መካከል 92 በመቶ የሚሆኑት በጤና ተቋማት ውስጥ እያገለገሉ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
"አዋላጅ ነርሶቹ ባሉበት ሙያ እንዲቀጥሉና የተሸለ ለውጥ ማምጣት እንዲቻል በየጊዜው ሥልጠና በመስጠት ብቃታቸው እንዲሻሻል ብሎም የሥራ አካባቢያቸውን ምቹ ማድረግ ያስፈልጋል" ብለዋል።
በሀገሪቱ ካሉት አዋላጅ ነርሶች መካከል 57 በመቶ የሚሆኑት በዲፕሎማ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ያስረዱት ምክትል ፕሬዝዳንቱ፤ የተሻለና ጥራት ያለው አገልግሎት ለማግኘት የትምህርት ደረጃቸውን እንዲያሻሽሉ እድል መፍጠር እንደሚገባም አመልክተዋል።
ለተግባራዊነቱ የመንግስት አካላት ፣ የትምህርት ተቋማትና የሌሎች ባለድርሻ አካላት ጥረት እንደሚያስፈልግ ጠቁመው በተለይ ለማህበሩ እያሳዩ ያሉትን አጋርነት ማጠናከር እንዳለባቸው ጠይቀዋል።
የኢፌዴሪ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ እንዳሉት፤ በአሁኑ ወቅት 3 ሺህ የሚሆኑ ሲቪል ማህበራት ተመዝግበው እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ጠቁመው ከማህበራቱ ውስጥ 280 የሚሆኑት የባለሙያዎች ባህበራት መሆናቸውን ናቸው።
እንደ ኢትዮጵያ ሚድዋይፈሮች ማህበር ያሉ የሙያ ማህበራት በሀገር ግንባታ ውስጥ ሊያበረክቱት የሚችሉት አስተዋፅኦ ከፍተኛ እንደሆነ የገለፁት አቶ ፋሲካው፤ የአባሎቻቸውን መብትና ጥቅም ከማስከበር ባለፈ በሀገሪቱ ሁለንተናዊ እድገት ላይ የበኩላቸውን ማሳረፍ እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።
ማህበራቱ በሀገር ደረጃ ውጤታማ የሆኑ ሥራዎችን እንዲሰሩ ኤጀንሲው አስፈላጊውን እገዛ በማድረግ እንደሚደግፍ አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ሚድዋይፈሮች ማህበር በተለይ የኮሮና ወረርሽኝ በጤና አገልግሎቱ ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥሮ በነበረበት ወቅት የእናቶችና ሕፃናት ጤና አገልግሎት እንዳይስተጓጎል የመገልገያ ቁሳቁሶችን ከማቅረብ ጀምሮ የተለያዩ ድጋፎችን ማድረጉን የገለጹት ደግሞ የደቡብ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ናፍቆት ብርሀኑ ናቸው።
ተግባሩ በሌሎች የጤና ዘርፎች ትልቅ መነሳሳት መፍጠሩንም ተናግረዋል።
"አንዲትም እናት በወሊድ ምክንት እንዳትሞት ሁላችንም የበኩላችንን አስተዋፅዖ ማበርከት ይገባናል" ያሉት አቶ ናፍቆት የክልሉ መንግስት የሰው ኃይል በማሰልጠን ፣ በቂ ግብዓት በማቅረብና መሠረተ ልማትን በማሟላ በዘርፉ የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጥ የሚጠበቅበትን ለመስራት ቁርጠኛ መሆኑን ጠቁመዋል።
የሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሠላማዊት መንገሻ በበኩላቸው በሀገሪቱ የተሟላ የእናቶችና ሕፃናት ጤና አገልግሎት ለመስጠት የሚያስፈልጉ 60 ሺህ አዋላጅ ነርሶች በመሆኑ፤ አሁን ያለውን እጅግ አነስተኛ ቁጥር ለማሳደግ ብዙ መስራትን ይጠይቃል ብለዋል።
በክልሉ በሚገኙ የጤና ሳይንስ ኮሌጆች ጥራቱን የጠበቀ ትምህርትና ሥልጠና በመስጠት የተሻለ አገልግሎት በሁሉም አካባቢዎች እንዲዳረሰ ለማድረግ ከማህበሩ ጋር ተባብሮ መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
በዝግጅቱ ላይ የፌዴራልና የሁለቱም ክልሎች የዘርፉ የሥራ ሀላፊዎች እንዲሁም ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ተገኝተዋል።