በህዝብና በመንግስት መካከል ትክክለኛ ግንኙነት ለመፍጠር እሰራለሁ --ኢዜማ - ኢዜአ አማርኛ
በህዝብና በመንግስት መካከል ትክክለኛ ግንኙነት ለመፍጠር እሰራለሁ --ኢዜማ
ሰቆጣ ግንቦት 8/2013 (ኢዜአ) በህዝብና በመንግስት መካከል ትክክለኛ ግንኙነት ለመፍጠር እሰራለሁ ሲል የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ ) አስታወቀ።
ኢዜማ በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር በሰቆጣ ከተማና አካባቢው ፕሮግራሙን በማስተዋወቅ የምረጡኝ ቅስቀሳ አካሂዷል።
የፓርቲው ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በወቅቱ እንደገለጹት ኢዜማ የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል የማህበራዊ ፍትህ ፓሊሲ ቀርፆ እየተንቀሳቀሰ ነው ።
"ሃገሪቱን አሁን ካለችበት ችግር ለማውጣት የዜጋ ፓለቲካን ማራመድ አማራጭ የለውም " ብለዋል።
በሃገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በሚከሰት ግጭት እየደረሰ ያለው የህይወት ጥፋት መፈናቀልና የንብረት ውድመት ሊፈታ የሚችለው በብሄር ፖለቲካ ሳይሆን በዜጋ ፖለቲካ መሆኑን አስታውቀዋል ።
ኢዜማ የፌደራል ስርአትን በአግባቡና በተገቢው መንገድ እንዲተገበር በማስቻል ዜጎች ራሳቸው በመረጡት መሪ ብቻ እንዲተዳደሩ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
"ፓርቲው በህዝብና በመንግስት መካከል እውነተኛ የሆነ ግንኙነት እንዲኖር ያደርጋል" ያሉት ፕሮፌሰር ብርሃኑ የማይፈፀሙና የማይተገበሩ ጉዳዮች ላይ ቃል እንደማይገባ አስታውቀዋል ።
በሰቆጣ የምርጫ ክልል ፓርቲውን በመወከል ለህዝብ ተወካዎች ምክር ቤት ለውድድር በእጩነት የቀረቡት አቶ አበባው ቴዎድሮስ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በመሪዎቿ ጥንካሬና በህዝቡ ሀገር ወዳድነት ወራሪ ሃይሎችን በጋራ በመመከት በቅኝ ሳትገዛ መቆየቷን አስታውሰዋል።
"ይህን መልካም እሴት ለማጎልበት ኢዜማ ሁሉም ዜጎች በእኩልነት የሚዳኙበትና የሚጠቀሙበትን ስርአት ይዘረጋል" ብለዋል።
ኢዜማ በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር የሚስተዋሉ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ባለ 21 ነጥብ የዋግ አጀንዳ ቀርፆ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስታውቀዋል።