ቀጥታ፡

በአዲስ አበባ በጎዴ፣ አሶሳ እና በሻሌ ሥም የተሰየሙ ሦስት ትምህርት ቤቶች ተመረቁ

አዲስ አበባ፤ግንቦት 07/2013 (ኢዜአ) በአዲስ አበበ ከተማ ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ውስጥ ጎዴ፣ አሶሳ እና በሻሌ በሚል የተሰየሙ ሦስት የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተመርቀው ለአገልግሎት በቁ።

ትምህርት ቤቶቹን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሃሰን መርቀዋል።

"ሪቫን እንጂ ተስፋ አንቆርጥም" በሚል ተገንብተው ለምረቃ የበቁት ትምህርት ቤቶች ጎዴ፣ አሶሳ እና በሻሌ የሚል ሥያሜ ተሰጥቷቸው ዛሬ ለአገልግሎት በቅተዋል፡፡የትምህርት ቤቶቹ ግንባታ በአጭር ጊዜ መጠናቀቁም ተገልጿል፡፡

ምክትል ከንቲባዋ አዳነች አቤቤ ሁለቱ ትምህርት ቤቶች በሶማሌ ክልል በምትገኘው "ጎዴ" ከተማና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ዋና ከተማ "አሶሳ" ተሰይመዋል፡፡

"ስያሜው ህብረ-ብሔራዊነትን አቅፋ የያዘችው የኢትዮጵያ መዲና አዲስ አበባ የሁሉም ስለመሆኗ አመላካች ነው" ብለዋል፡፡

ፕሮጀክቶችን ማስመረቅ ብቻ ሳይሆን ትውልድ የሚቀረጽባቸው እንዲሆኑም አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረገ ነው ምክትል ከንቲባዋ የተናገሩት፡፡

ስያሜዎቹ ተማሪዎች ከተሞቹ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ያበረከቱትን ጉልህ አስተዋጽኦ እንዲረዱ የሚያደርግ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳዳር ሙስጠፌ መሃመድ በበኩላቸው የከተማ አስተዳደሩ በጎዴ ከተማ ስም ትምህርት ቤት በማስገንባቱ መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡

"ይህ ከተማ አስተዳደሩ ያከናወነው ተግባር በኢትዮጵያ እውነተኛ ብዝሃነት እየመጣ ስለሆኑ ማሳያ ነው" ብለዋል፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አሻድሊ ሃሰን ከተማ አስተዳደሩ በክልሉ ዋና ከተማ "አሶሳ" ስም ትምህርት ቤት በመገንባቱ ደስታቸውን ገልጸዋል፡፡

ይህ ተግባር ከዚህ ቀደም ለይስሙላ የነበረው ፌዴራሊዝም ወደ እውነተኛ ፌዴራሊዝም መሸጋገሩን ማሳያ መሆኑን ነው ያመለከቱት፡፡

ርዕሳነ መስተዳድሮቹ አገሪቷ በበርካታ ፈተናዎች ውስጥ ብትሆንም ለፈተና የማትንበረከክና ልማት በማካሄድ ለህዝቦች ተጠቃሚነት የምትስራ መሆኗን ገልዋል።

ዘንድሮ የሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሁሉም ህብረተሰብ የአካባቢውን ሰላም መጠበቅና ከሃሰት ፕሮፓጋንዳ መጠበቅ እንዳለበትም ገልጸዋል፡፡

በምረቃ መርሃ ግብሩ የአዲስ አበባ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች፣ መምህራን፣ ተማሪዎች እና የተማሪዎች ወላጆች ታድመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም